ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር የማግባባት (Lobyying) ስራ ከሚሰራ ኩባንያ ጋር የ1.8 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረመች

ኢሳት (የካቲት 6 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት በተያዘው የፈረንጆች አመት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የማግባባት (ሎቢንግ) ስራ ከሚያካሄድ አንድ ድርጅት ጋር የ1.8 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት መፈራረሙ ታወቀ።

በዚሁ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ግርማ ብሩ መንግስትን በመወከል SRG-LLC ከተሰኘ ኩባንያ ጋር የፈረሙት ሰነድ የውጭ ወኪሎችን ጉዳይ የሚዘግበው ፎሪን ኤጀንትስ ሬጂስትሬሽን በድረ-ገጹ ላይ ባፈረው መረጃ አመልክቷል።

በዚሁ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ከአሜሪካው ኩባንያ በየወሩ 150ሺ ዶላር ክፍያን በመክፈል ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እንደሚደረግ ለመረዳት ተችሏል።

ከኩባንያው ጋር የተፈረመው ይኸው ስምምነት የአሜሪካ የምክር ቤት አባላትን በማግባባት በፖሊስ እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ የምታነሳቸው አጀንዳዎች ትኩረት እንደሚያገኙ ኩባንያው በተያዘው አመት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያካሄድ ታውቋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ሃገራት መካከል ለተመሳሳይ ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብን በመመደብ ከግብፅና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተወዳዳሪ መሆኗን አፍሪካ ኢንተሊጀንስ የተሰኘ የደህንነት ተቋም ባለፈው አመት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ-ኦባማ አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግስት ለሎቢንግ ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። በአሜሪካ በቅርቡ የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎም ኢትዮጵያ SRG-LLC ከተሰኘው ኩባንያ ጋር ለአንድ አመት የሚዘልቅ ስምምነት ደርሳለች።

በአሜሪካ ህግ መሰረት ማንኛውም የአሜሪካ ኩባንያ ከውጭ መንግስት ጋር የሚያደርጉትን ስምምነት ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሲሆን የዚሁኑ ስምምነት ምክንያት በማድረግ ኩባንያው የደረሰውን ስምምነት ለመዝጋቢው ተቋም አስረክቧል።

በፈረጆቹ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ መንግስትና በሎቢንግ ኩባንያው መካከል የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያ በየሶስት ወሩ ክፍያን እንዲፈጸም የሚያዝ ሲሆን፣ ገንዘቡም በዌልስ ፋርጎ ባንክ በኩል ገቢ እንዲያደርግ በሰነዱ ተመልክቷል።

የማግባባት ስራውን ለማከናወን ስምምነት የደረሰው ኩባንያ በበኩሉ ኢትዮጵያን በመወከል የመገኛኛ ብዙሃንን ጨምሮ የፖሊሲና የተለያዩ የቢዝነስ ጉዳዮች በአሜሪካ በኩል ትኩረት እንዲያገኙ የማግባባት ስራን እንደሚያከናውን በዶክመንቱ አስፍሯል።

ይኸው በሚስተር ግሬግ ሎሙማን የተፈረመው ስምምነት የተለያዩ ተጨማሪ ወጪዎች በሚኖሩ ጊዜ ደንበኛ ወይም የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፍን ገልጿል።

በአሜሪካ ህግ ይፋ እንደሚያደርጉ ከሚጠየቁ መረጃዎች ውጭ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረጉ ልውውጦችም ሚስጢራዊ ሆነው እንደሚቆዩ በሰነዱ ተመልክቷል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የምክር ቤት አባላት በሎቢንግ (በማግባባት) ስራ እንዳይሰማሩ አዲስ ህግ ተግባራዊ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ 11ሺ 143 የተመዘገቡ የሎቢስት አካላት የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚሁ ግለሰቦች የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና መንግስታትን በመወከል ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያላቸው ጥቅም እንዲጠበቅ የማግባባት ስራዎችን እንደሚያከናውኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።