ኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ

(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 1/2010) የኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ።

ትብብሩን ለማስፋት በተያዘው እቅድ መሰረትም የኢትዮጵያ፣የኤርትራና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ጅቡቲ ገብተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከ1990 ጀምሮ ለ20 አመታት ተዘግቶ የነበረው በአስመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ በሁለቱ ሃገራት መሪዎች በይፋ ተከፍቷል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሐመድ አብድላሂ (ፎርማጆ) አስመራ ላይ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ባደረሱበት ባለ 4 ነጥብ ስምምነት፣ የሃገሪቱን ህዝቦች ትብብር ለማጠናከርና የባህል፣ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የጸጥታ ትብብር ለማድረግ እንዲሁም ለአከባቢው ሰላም በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ተመክቷል።

የተደረሰባቸውን ስምምነቶች የሚከታተልና ወደ ስራ የሚተረጉም የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

ሐገራቱ አንደኛቸው የሌላኛውን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲሁም ነጻነት ለማክበር መስማማታቸውም ተመልክቷል።

የሶስቱ ሃገራትን መሪዎች ስምምነትን ተከትሎ ትብብሩን ለማስፋትና ጅቡቲን የሂደቱ አካል ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ፣የኤርትራና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ ወደ ጅቡቲ ተጉዘዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ለሁለት ቀናት ጉብኝት ኤርትራ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር በመሆን 20 አመታት ተዘግቶ የቆየውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ዛሬ በይፋ ከፍተዋል።

ግንቦት 4 ቀን 1990 የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ ሁለቱም ሃገራት በአዲስ አበባና በአስመራ የነበራቸውን ኤምባሲ መዝጋታቸው ይታወሳል።

በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ አውአሎም ወልዱና በኢትዮጵያ የኤርትራ የኤርትራ አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ አስመሮም በወቅቱ ወደ የሃገሮቻቸው ተመልሰዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በይፋ መከፈቱ ይታወሳል።

አቶ ሰመረ ርዕሶም በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር ሆነው ሲሾሙ አቶ ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውም አይዘነጋም።