ኢትዮጵያውያን በተለይም ቄሮዎችና ፋኖዎች ሊወደሱ ይገባል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 5/2010)በኢትዮጵያ ነጻነት እንዲመጣ መስዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያውያኖች በተለይም ቄሮዎች ፋኖዎች ሊወደሱ እንደሚገባ አክቲቪስት ታማኝ በየነ ገለጸ።

አክቲቪስት ታማኝ በየነ ይህን መልዕክት ያስተላለፈው በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚያደርገውን ጉብኝት በመቀጠል በሳምንቱ መጨረሻ ከአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ቆይታ ነው።

አክቲቪስት ታማኝ በየነ ሕዝባዊውን ትግል አስተባብረው የጨለማው ዘመን እንዲያበቃ ፊት ለፊት ለተጋፈጡት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና በአጠቃላይ ለለውጡ ቡድን ያለውን ክብር ገልጿል።

በአዳማ ስታዲየም ከፍተኛ ሕዝብ በታደመበት ስነስርአት የኦሮሞ ባህላዊ ልብስን በመልበስ ከባለቤቱ ድምጻዊት ፈንትሽ በቀለ ጋር የተገኘው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ኢትዮጵያ እንደሃገር የቆየችው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት መሆኑን ገለጿል።

የሁሉም ባህልና ቋንቋ ለተከበረባት አንዲት ኢትዮጵያ ሁሉም እንዲነሳ ጥሪውን አቅርቧል።

ሕዝብን የሚከፋፍሉ ወገኖች ኦሮሞና አማራ እሳትና ጭድ ናቸው ማለታቸውን በማስታወስ ኦሮሞና አማራ እሳትና ጭድ ሳይሆኑ እጅና ጓንት ናቸው በማለት የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ጥሪውን አቅርቧል።

በአዳማ ስታዲየም የተገኙት ኢትዮጵያውያን የአማራ ደም የእኔ ደም ነው፣የትግራይ ደም የእኔ ደም ነው፣ ኢትዮጵያዊ ደም የኔ ደም ሲሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።

ከሳምንት በፊት ከ22 አመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው አክቲቪስት ታማኝ በየነ በተለያዩ መድረኮች ከኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይቷል።

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንዲሁም በብሔራዊ ቲያትር በባህርዳር፣በጎንደር፣ደብረታቦርና በቤተሰቦቹ መኖሪያ ጋይንት ከኢትዮያውያን ጋር በአደባባይና በአዳራሽ ተወያይቷል።

በአዳማ የቀጠለው ሕዝባዊ ስብሰባ ወደ ሌሎች ከተሞች እንደሚቀጥልም መረዳት ተችሏል።