ኢትዮጵያውያን ከእርስ በርስ ሽኩቻ እንዲወጡ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 14/2011)ኢትዮጵያውያን ከእርስ በርስ ሽኩቻ ወተው በአንድነት በመሆን ለሃገራቸው ሰላም እንዲንቀሳቀሱ ብጹእ ዶክተር አቡነ ኤዎስጣጢዮስ ጠየቁ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብጹእ ዶክተር አቡነ ኤዎስጣጢዎስ ከ10 አመታት ስደት በኋላ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዛቸው በፊት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው ሰላምና አንድነት በጋራ እንዲቆሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ብጹእ አቡነ ኤዎስጣጢዎስ በ1997 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በመንግስት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን አባል በነበሩበት ወቅት መንግስት ከመጠን ያለፈ ሃይል ተጠቅሟል የሚል አቋም በመያዛቸው ከአቡነ ጳውሎስ ጭምር ግሳጼ ደርሶባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ብጹእ ዶክተር አቡነ ኤዎስጣጢዎስን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጽሕፈት ቤታቸው ድረስ በመጥራት ካሳሰቧቸው የኮሚስኑ አባላት አንዱ ነበሩ።

በምዕራባዊው የአሜሪካ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ በመሆን በሳክራሜንቶና ሲያትል መቀመጫቸውን አድርገው የቆዩት ብጹእ አቡነ ኤዎስጣጤዎስ፣ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ባለመግባባት በቀጣዩም ፓትሪያርክ በአቡነ ማቲያስ ችግሩ ባለመፈታቱ በስደት ላይ ቆይተዋል።

ከ10 አመታት ስደት በኋላ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸውን በተመለከአ በወቅቱ ሁኔታ ላይ ያነጋገርናቸው ብጹእ አቡነ ኤዎስጣጤዎስ ኢትዮጵያውያን ከብሔረሰብ ልዩነትና ውዝግብ እንዲሁም ግጭት ርቀው በአንድነት ለአንዲት ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹእ አቡነ ኤዎስጣጤዎስ ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝብን መለያየትና ግጭትን መፍጠር የሰይጣን ተግባር ነው ብለዋል።

ብጹእ ዶክተር አቡነ ኤዎስጣጤዎስ ዛሬ መስከረም 14/2011 ከ10 አመታት ስደት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል።