ኢሳት አፈና ተቋቁሞ በአየር ተመለሰ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የተሰጠ መግለጫ

ኢሳት አፈና ተቋቁሞ በአየር ተመለሰ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የተሰጠ መግለጫ
የካቲት 3፣ 2003ዓም
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ከህዳር 23 2003 ዓም ጀምሮ ላለፉት ሁለት ወራት ስርጭቱን በታይኮም 5
ሲያስተላለፍ መቆየቱ ይታወሳል። በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ይህን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማፈን ያለፉትን ሁለት
ወራት ላይ ታች በማለት አሳልፎአል። ገዢው ፓርቲ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሦስት ሚሊዮን ህዝብ ለከፍተኛ የረሀብ
አደጋ በተጋለጠበጥ ወቅት፣ በድሀ ህዝብ ሥም በልመና የተገኘን የውጭ ምንዛሪ፣ ኢሳትን ለማፈን ተግባር እንዲባክን
አድርጎታል።
የኢሳት ልጆችና የኢሳት ደጋፊዎች አስቀድሞ ከራሱ ከመንግስት ባለስልጣናት በደረሳቸው መረጃ መሰረት አማራጭ
የመውጫ መንገዶችን ሲፈልጉ ከርመዋል። በኢሳት ልጆች ጥረት ሙከራው ተሳክቶ በ24 ሰአት ውስጥ ያን መተንፈሻ
ያጣ ህዝብ መተንፈሻ ቀዳዳ ሊሆኑት እንደገና በኢንቴል ሳት 10 (Intelsat 10 at 68.5 East ፣ Cband ፣
Transponder 14 ፣ Downlink: 3808 V ፣ Symbol rate: 10340 ፣ FEC: ¾) ስርጭት መልሶ ጀምሯል።
በዚህ አጭር ጊዜ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ በሺ የሚቆጠሩ የስልክ መልእክቶች ደርሰውናል። ሁሉም መልእክቶች
በርትተን እንድንሰራ፣ በሁለትና በሶስት የማሰራጫ ጣቢያዎች ስርጭታችንን እንድናስተላልፍ የሚጠይቁ ናቸው።
አሁን ከአጭር ቀናት መቋረጥ በሁዋላ ተመልሰን መምጣታችን ለእኛ እንደታላቅ ድል ሊቆጠርልን ይችል ይሆናል። ያ
ግን አይደለም። ይህ ድል የእኛ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ድል ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ይዞ የተሸነፈ ሀይል የለም።
ታሪክ ምስክር ነውና።
አሁንም ድላችን ገና ነው። የድላችንን ሻማ የምናበራው የፕሬስና ሌሎች ነጻነቶች በአገራችን ሰፍነው ስናይ ብቻ ነው።
ይህ እስከሚሆን ድረስ እየወደቅን እየተነሳን ትግላችን እንቀጥላለን።
ውድ ኢትዮጵያውያን – መንግስት እየሄደበት ያለው የተሳሳተ መንገድ ይበልጥ እንድንሰራ ይበልጥ እንድንታገል፣
ይበልጥ ሀሳብን የመግልጽ ነጻነትን ምን ያክል ውድ ነገር መሆኑን እንድንረዳ የሚያደርገን ነው።
በመጨረሻም
1ኛ በውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን የኢሳትን የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም በመደገፍ ኢሳት ይበልጥ ተጠናክሮ
እንዲወጣ እንድታደርጉ በአገር ውስጥ ባለው ህዝባችን ስም እንጠይቃችሁዋለን።
2ኛ በአገር ቤት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ያላችሁ በገንዘብ፣ መረጃ ማግኘት የምትችሉ መረጃ በመስጠት ድጋፍ
እንድትሰጡን እናንተንም በአክብሮት እንጠይቃለን።
3ኛ የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት፣ እንኳንስ በጀግንነታቸው ታሪክ የመሰከረላቸውን ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን
ከጎናችን አሰልፈን ይቅርና ጥቂቶች ሆነን የሀሳብ ነጻነትን ብቻ በመያዝ አሸንፈን እንደምንወጣ እናውቃለን። ማንም
ከሀሳብ ነጻነት ጋር ተፋልሞ ያሸነፈ የለም። ዘመኑ የሀሳብ ነጻነት አሸንፎ የወጣበት ዘመን ነው። በዚህ መረጃ እንደልብ
በሚገኝበት ወቅት ለህዝብ መረጃ እንዳይደርስ የምታደርጉትን መሯሯጥ እንድታቆሙ ጥሪ እናቀርባለን።
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ልሳን ነው
የኢሳት ስራ አመራር
www.ethsat.com