አዲስ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሊሾም

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 21/2011) የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ተነስተው በምትካቸው አዲስ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እንደሚሾም ተገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ እንዳስታወቀው ፓርላማው በነገ ውሎው አዲስ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ይሾማል።

በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን የሚያገለግሉት አቶ ዳኜ መላኩ በፖለቲካ አመለካከታቸው በተከሰሱ ንጹሃን ላይ በሕግ ስም የፖለቲካ ውሳኔ ሲያሳልፉ የቆዩና ከፍተኛ ትችት የሚቀርብባቸው ዳኛ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

የፖለቲካ ጉዳዮች የይግባኝ ፋይሎችን በብቸኝነት በሰብሳቢ ዳኝነት ሲመሩ መቆየታቸውም ተገልጿል።

ፕሬዝዳንቱ አቶ ዳኜ መላኩ ከሙያቸው ይልቅ ለስርአቱ ፍጹም ታማኝ ሆነው መቆየታቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

የቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ በፓርላማው በሰኔ 2008 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት አቶ ዳኜ መላኩ ላለፉት 2 አመታት ከመንፈቅ ያህል በዚህ ስፍራ ቆይተዋል።

በዕለቱ ምክትል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ጸጋዬ አስማማው ደግሞ በግልጽ የሕወሃት አባል የነበሩና ሕወሃትን ወክለው የፓርላማ አባል የነበሩ መሆናቸውም ታውቋል።

አቶ ጸጋዬ አስማማው የተኩት አቶ መድህን ኪሮስን እንደነበርም ታውቋል።

አቶ መድህን ኪሮስ ደግሞ የሕወሃት አባል ብቻ ሳይሆኑ የሕወሃት ታጋይ እንደነበሩም ከሕይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።

በሕጉ መሰረት ዳኞች የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ የተከለከለ ቢሆንም በኢትዮጵያ እስከዛሬ የነበረው ይህንን ተግባራዊ ሳያደርግ ቆይቷል።

አቶ ዳኜ መላኩንና አቶ ጸጋዬ አስማማውን ሽሮ አዲስ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ለመሾም ፓርላማው ለነገ ቀጠሮ መያዙንም ፓርላማው በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል።