አክቲቪስት ታማኝ በየነ ተፈናቃዮችን ጎበኘ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 3/2011) አክቲቪስት ታማኝ በየነ በድሬደዋ ከተማ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮችን ዛሬ ጎበኘ።

የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሒም ኡስማን በተገኙበት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል።

በእግረኛ የሙዚቃ ቡድን አቀባበል የተደረገለት አክቲቪስት ታማኝ በየነ የኢትዮጵያዊነትና የፍቅር ተምሳሌት የሆነችውን ድሬደዋን ከነበረችበት ተጎሳቁላ በማግኘቱ ማዘኑን ገልጿል።

አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከ30 አመት በፊት የሚያውቃት ድሬደዋ፣የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው ሕዝቧ 27 አመታት በሐገሪቱ ውስጥ በነበረው የጥፋት ጉዞ ሰለባ መሆኑን አመልክቷል።

አሁን ላይ የታየው ለውጥ እንዲመጣ መስዋዕትነት ለከፈሉ ሁሉ በተለይም ለፋኖዎች፣ለቄሮዎች፣ለዘርማዎችና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አክብሮቱን የገለጸውና ሕዝቡም አክብሮቱን እንዲሰጥ የጠየቀው ታማኝ በየነ መከራችን እንዲያበቃና ነጻነት እንዲመጣ የከፈሉትን ዋጋ አመስግኗል።

የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሒም ኡስማን በተገኙበት በድሬደዋ ከተማ ብዙ ሕዝብ በታደመበት ትዕይንተ ሕዝብ ላይ እንደሁልጊዜው ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን የሰበከው አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሁሉም ሃይማኖት ቋንቋና ባህል የተከበረባት ፣ማንም ከማንም የበላይ የማይሆንባት ኢትዮጵያን በአንድነትና በጽናት እንጠብቃት ሲል ጥሪ አቅርቧል።