አንድ የእስራኤል ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ክስ መሰረተ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 2/2010) አንድ በኢትዮጵያ በማእድን አሰሳ ላይ የነበረ አንድ የእስራኤል ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ክስ መሰረተ።

ዘሔግ ኔዘርላንድ በተመሰረተው በዚህ ክስ አይ ሲ ኤል የተባለው የእስራኤል ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት የ198 ሚሊየን ዶላር ካሳ መጠየቁም ተመልክቷል።

የእስራኤሉ ኩባንያ አይ ሲ ኤል በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በኔዘርላንድ ዘሔግ ክሱን የመሰረተው ስምምነቱ የተካሄደው በኔዘርላንድ በመሆኑ እንደሆነም አስታውቋል።

በኢትዮጵያና በኔዘርላንድ መካከል የተፈረመውን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ከለላ ስምምነት የጣሰ ድርጊት እንደሆነም አክሏል።

አላና ፖታሽ የሚባል የካናዳ ኩባንያ በኢትዮጵያ የአፋር ክልል የጀመረው የፖታሽ ማእድን አሰሳ በመሳካቱ ለ5 አመታት የ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ቶን የፖታሽ ማዕድን ክምችት መኖሩን አረጋግጦ የማዕድን ልማቱን ለማከናወን እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 ስምምነት መፈራረሙን የሪፖርተር ዘገባ ያስታውሳል።

ሆኖም ይህ ኩባንያ ማዕድን ለማልማት የሚያስችለውን የ700 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ማቅረብ ባለመቻሉ አይ ሲ ኤል የተባለው የእስራኤል ኩባንያ ስራውን መረከቡን ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

ይህንን የ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ቶን ፖታሺየም ማእድን ስራ ላይ ለማዋል በኔዘርላንድ ዘሔግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት የፈረመውና በ150 ሚሊየን ዶላር ግዢውን የፈጸመው የእስራኤሉ ኩባንያ አይ ሲ ኤል በኢትዮጵያ መንግስት ደረሰብኝ ባለው ጫና በጥቅምት ወር 2009 ስራውን አቋርጦ ከኢትዮጵያ መውጣቱ ተመልክቷል።

የፖታሽ ማዕድን ማውጫና የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን በ3 ቢሊየን ዶላር በመገንባት ስራውን በስፋት ለማካሄድ በመንቀሳቀስ ላይ ሳለ መንግስት ሕገ ወጥ ግብር እንድከፍል ጠይቆኛል በቂ መሰረተ ልማትም ለመዘርጋት አልቻለም በሚል ውሉን አቋርጧል።

በዚህም ለደረሰበት ኪሳራ የ198 ሚሊየን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ዘሄግ ኔዘርላንድ ላይ ክስ መመስረቱ ታውቋል።