አንዳርጋቸው ጽጌ አስመራ ገቡ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 11/2010) አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ አስመራ ገቡ።

አቶ አንዳርጋቸው የመን ሰንአ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ታግተው ለአራት አመታት ያህል በወህኒ ቤት ማሳለፋቸው ይታወሳል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን ላይ የታገቱት ወደ አስመራ በመጓዝ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደነበርም ይታወሳል።

የምርጫ 1997 ሰላማዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በሃይል ከተጨፈለቀ በኋላ ብዙዎች ከትግሉ ሜዳ ሲወጡና ከእንስቃሴ ሲገደቡ ትግሉን በሃይል ጭምር ማስቀጠል ይገባል በሚል ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ግንቦት ሰባትን የመሰረቱት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ነበሩ።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኤርትራ በረሃ ውስጥ የአመጽ ትግሉን ለማደራጀት ለአመታት በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ማለፋቸውም ታውቋል።

የኤርትራውን ትግል በቅርብ ሆነው ሲመሩ የቆዩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከዩናይትድ አረብ ኢምሬት ወደ አስመራ ሲጓዙ ሰኔ 16/2004 የመን ላይ በየመን የጸጥታ ሃይሎች መታገታቸው ይታወሳል።

ለአራት አመታትም በታወቀና ባልታወቀ ወህኒ ቤት ያሳለፉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ግንቦት 20/2010 ከወህኒ መፈታታቸው ይታወሳል።

በማግስቱ ግንቦት 21/2010 በቤተመንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መወያየታቸውም አይዘነጋም።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኤርትራ ቆይታቸው በበረሃ የሚገኙ የትግል ጓዶቻቸውን ያገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።