አቶ ፍጹም አረጋ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ተተኩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 26/2011) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ መተካታቸው ተገለጸ።

አቶ ፍጹም አረጋ ለሌላ የስልጣን ቦታ መታጨታቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ከነገ ማክሰኞ ጥቅምት 27/2011 ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ሃላፊነትን ስራ የሚጀምሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል መሆናቸውም ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ግዜ ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ያገለገሉት አቶ ፍጹም አረጋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እሳቸውን እንደሚተኳቸውና ከነገ ጀምሮ ስራ እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር ለተደራጀው የፕሬስ ክፍል ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም በሴክሬታሪያትነት መሾማቸውም ተመልክቷል።

የፕሬስ ሴክሬተሪዋ ቀደም ሲል በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ይሰሩ የነበሩ ተግባራትን እንደሚከውኑም ተገልጿል።

አቶ ፍጹም አረጋ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ቦታውን እንደለቀቁም በማህበራዊ ገጻቸው ላይ ዛሬ አስታውቀዋል።