አቶ ጌታቸው አሰፋ በኢሕአዴግ ጉባኤ መክፈቻ ላይ አልተገኙም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 23/2011) ለሕወሃት ስራ አስፈጻሚነት የተመረጡ የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በኢሕአዴግ ጉባኤ መክፈቻ ላይ እንዳልተገኙ ተነገረ።

በፌደራል መንግስት የእስር ማዘዣ እንደወጣባቸው ሲነገርባቸው የቆዩት አቶ ጌታቸው አሰፋ በሕወሃት ስራአስፈጻሚ ሆነው መመረጣቸው ብዙዎቹን እያነጋገረ ይገኛል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ ላለፉት 18 አመታት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ ለተፈጸሙ መንግስታዊ ግድያዎችና በዜጎች ላይ ለደረሱ ሰቆቃዎች ተጠያቂ ናቸው።

ከስልጣን ከወረደ በኋላም በሃገሪቱ አለምረጋጋት እንዳይፈጠር በተፈጸሙ ጥቃቶች እጃቸው እንዳለበት ይጠራጠራሉ።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በብዙዎች ዘንድ ስውሩ ሰው በሚል ይታወቃል።

በየትኛውም መገናኛ ብዙሃን የማይቀርቡትና በአደባባይ የማይታዩት የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ ፎቶአቸው በይፋ እንዳይታይም ሰደረግ ቆይቷል።

በህወሃት የ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን በተፈጸሙ መንግስታዊ ግድያዎችና ሰቆቃዎች ዋነኛ ተጠያቂ ተደርገው ይወሰዳሉ።

ይህ ብቻ አይደለም ከስልጣን ከወረዱ በኋላም በእነ ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ እንቅልፍ የላቸውም የሚባሉት ጌታቸው አሰፋበመቀሌ መሽገው እንደሚገኙ ይነገራል።

በፌደራል መንግስቱ የእስር ማዘዣ እንደወጣባቸው የሚነገርላቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ ባለፈው ጊዜ ከመቀሌ ወደ ሱዳን አምርተው እንደነበርም የኢሳት ምንጮች ገልጸው ነበር።

አቶ ጌታቸውን በተመለከተ በወቅቱ የተጠየቁት የህዉሃት ምክትል ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዜአብሔር ለተከታታይ 15 ቀናት እንዳላዩኣቸውና በዚያን ሰዓትም የት እንዳሉ እንደማያውቁ መናገራቸውም ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ ኣንዳለም ባልተጠበቀ ሁኔታ የህዉሃት ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተመረጡት አቶ ጌታቸው አሰፋ በሃዋሳ በተከፈተው የኢህአዴግ ጉባኤ አለመገኘታቸው ተነግሯል።

የኢሳት ምንጮች እንዳሉት አቶ ጌታቸው አሰፋ መገኘት በሚጠበቅባቸው የኢህአዴግ ጉባኤ አለመገኘታቸው በፌደራል መንግስቱ እንደሚፈለጉና ስጋት እንዳለባቸው ማረጋገጫ ሆኗል።

እራሳቸውን በተመለከተ የተጠየቁት የህዉሃት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ ይፋዊ መግለጫ ሳይኖር ሚዲያዎች ሃሜት ማውራታቸው ትክክል አይደለም ብለዋል። በአቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ክስ ስለመመስረቱም የማውቀው ነገር የለም ነው ያሉት።

የቀደመውን የደህንነት ሃላፊ ፈልጎ ህዉሃት ጋር የመጣ የመንግስት-አካልም አለመኖሩን ገልጸዋል።

እናም አቶ ጌታቸው አሰፋ አውሮፕላን ካላመለጠው በኢህአዴግ ጉባኤ ይገኛል ሲሉም ነው የተናገሩት።

ይህም ሆኖ ግን አቶ ጌታቸው አሰፋ በጉባኤው ላይ ባለመታየታቸው የእርሳችው ነገር አሁንም ያልተፈታ እንቆቅልሽ እንደሆነ ይገኛል።