አቶ ደመቀ መኮንን የእኔ ስም ሆን ተብሎ ተጠቅሷል አሉ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 17/2011) ለሱዳን ተላልፎ በተሰጠው መሬት ላይ የእኔ ስም ሆን ተብሎ ተጠቅሷል ሲሉ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ለበርካታ አመታት ለሱዳን ከተሰጠው መሬት ጋር በተያያዘ በፊርማቸው አስረክበዋል ተብለው ሲወቀሱ የነበሩት የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ከአማራ መገናኛ ብዙሃን  ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጉዳዩ ሲፈጸም እኔ ከሀገር ውጭ ነበርኩ ብለዋል።

በወቅቱ ምንም እውነታ የሌለው የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተፈጽሞብኛል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን።

አለአግባብ ለሱዳን ተላልፎ በተሰጠው መሬት ጉዳይ የተለየ አቋም ነበረን ሲሉም ገልጸዋል።

ለሱዳን ተላልፎ ተሰጥቷል በተባለው መሬት ጉዳይ ላይ ለበርካታ ዓመታት ስማቸው ሲነሳ ነበር።

በድብቅ መሬቱን በፊርማቸው ያስረከቡት እሳቸው ናቸው ከሚለው መረጃ ጋር ሲጠቀሱ የነበሩት አቶ ደመቀ መኮንን የነበረውን እውነታ በይፋ ገልጸዋል።

በቅርቡ በወጣ አንድ ሰነድ ተሰጠ የተባለውን መሬት በፊርማቸው ያስረከቡት የህወሀቱ አቶ አባይ ጸሀዬ መሆናቸው መዘገቡ የሚታወስ ነው።

ለአማራ መገናኛ ብዙሃን ቃለመጠይቅ የሰጡት ምክትል ጠቅልላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ማድረጉ ጠቃሚ ነው  ብለዋል።

ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበርን በተመለከተ ከሚኒሊክ ጀምሮ ሲሰራ የቆየ አካሄድ አለ፤ ይሁን እንጅ ከሚነሳብኝ ቅሬታ አንፃር በወቅቱ ጉዳዩ ሲፈጸም እኔ የነበርኩት እንግሊዝ ሀገር ነው ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን ብዙ ጊዜ ሲወራ የምሰማው ደመቀ ለሱዳን መሬት ሰጥቶ ከፍተኛ ሹመት አገኘ የሚል ነበር ሲሉ በማስታወስ ገልጸዋል።

የእኔ የስልጣን እድገት የተሰጠኝን ሃላፊነት በአግባቡ ከመፈጽም ጋር በተያያዘ ባስመዘገብኩት ውጤት እንጂ አለአገባብ በተጠቀሰው ግይዳይ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

‹‹ምንም እውነታ የሌለው የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው የተፈጸመብኝ፡፡ይህ ሆን ተብሎ አንገቴን እንድደፋ እና አመራርነቴም ተቀባይነትን እንዳያገኝ የተደረገ ሴራ ነው፡፡›› ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን።

በወቅቱ ለሁኔታው ትኩረት አለመስጠቴ እንደስህተት ሊወሰድ ይችላል ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን አንድም መሬት አልተሰጠም እየተባለ የተካሄደው የድንቁርና አካሄድ እኔም ድርጅቱም ልንማርበት የሚገባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የእኛ አመራርነት ጎልቶ እንዳይወጣ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ተጠቅመውበታል በማለት የገልጸኡት አቶ ደመቀ መኮንን እነዚያ ሰዎች እነማን እንደሆኑ በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

በወቅቱም ቢሆን አለአግባብ ለሱዳን የተሰጠው  መሬት ተገቢ አይደለም የሚል አቋም ነበረን።

ወደፊትም ማስተካከያ እንዲወሰድበት እንሰራለን በማለት ተሰጥቷል በተባለው መሬት ጉዳይ ብአዴን ጠንካራ አቋም እንዳለው ገልጸዋል።