አቶ ዛዲግ አብርሃ ከድርጅታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2011)ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕውሃት/ ከለውጡ በተቃራኒው በሚያደርገው ጉዞ እና በራያ ህዝብ ላይ በሚያደርሰው በደል ሳቢያ ከድርጅቱ በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዲሞክራታይዜሽን ማዕከል አስተባባሪ በመሆን የሚያገለግሉት አቶ ዛዲግ አብርሃ ለሕወሃት ያስገቡት 5 ገጽ ማመልከቻ ኢሳት ደርሶታል።

ቀደል ሲል የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ድኤታና የፍትህና የህግ ስርዓት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዛዲግ አብርሃ “ለሕዉሃት ልዩ ዞን ጽሕፈት ቤት” በሚል አዲስ አበባ ለሚገኘው የሕዉሃት ጽሕፈት ቤት የስንብት ደብዳቤ አስገብተዋል።

አቶ ዛዲግ ርሳቸው ከራያ ህዝብ ውስጥ በመውጣታቸው በጥርጣሬ ሲታዩ መቆየታቸውን አስታውሰው ወጣትነትም በህዉሃት ውስጥ ላለመታመን ምክንያት መደረጉን ተናግረዋል።

ሕወሃት ውስጥ ይደግፏቸው የነበሩ ጥቂት ሰዎች እንደነበሩ የተጠቀሱት አቶ ዛዲግ አብርሃ የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ደሊቨር ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ከህዉሃት ጋር ትልቅ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መወሰኑን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ  ጽሕፈት ቤት ማህበራዊ ገጽ ላይ ይኸው የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ በመጻፉ ለምን የፖለቲካ እስረኞች ተብሎ ቀረበ በሚል ጥቃትና ዛቻ እንደደረሳቸው አመልክተዋል።

የህወሃት አመራሮች በፖለቲካ እስረኞች መፈታት አለመደሰታቸውን ይልቁንም መቆጨታቸውንም አስፍረዋል።

አቶ ዛዲግ አብርሃ ሕዝባዊ ወያኔ ከመጣው ለውጥ ጋር አብሮ ለመሄድ አለመፍቀዱ ይልቁንም በተቃራኒ አቅጣጫ መጓዙ ድርጅቱን ለመሰናበት ምክንያት እንደሆናቸውም አስረድተዋል።

ለውጡ የትግራይ ሕዝብንም ሆነ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚጠቅም ቢሆንም ህወሃት በጥቂት ጠባብ ፀረ-ለውጥ ቡድን ተጠልፎ ከሃገራዊ ለውጥ ጎን መሆን አለመቻሉን ተችተዋል።

ይህም ለጥቂት የህወሃት ባለስልጣናት ጥቅም ሲባል ህወሃት አፍራሽ ተግባር ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት አንድ የሆኑትና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዲሞክራታይዜሽን አስተባባሪ “ሕዉሃት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እየተወሰደ ያለውን ትክክለኛ ርምጃ በመቃወም የገባበት ግዙፍ ስህተት ከድርጅቱ ጋር እንዳልቀጥል ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱ ነው ብለዋል”።

የራያ ህዝብ ያለፈቃዱ በመካለሉ ሳቢያ ባሰማው ተቃውሞ ሲሰደድና ሲገደል ኖሯል ያሉት አቶ ዛዲግ አብርሃ ባልተደራጀ መንገድ የነበረው ተቃውሞ ለጥቃት አጋልጦት መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን የራያ ህዝብ በተደራጀ መንገድ ወደ ትግል ገብቷል ያሉት አቶ ዛዲግ አብርሃ በዚህ ህዝብ ላይ በህጻናት ላይ ጭምር የሚፈጸምበት ጥቃት ከህዉሃት ለመሰናበት ለውጡ ምክንያት እንደሆናቸውም በጽሁፋቸው አብራርተዋል።

አቶ ዛዲግ አብርሃ በመጨረሻም ለህወሃት ጽሕፈት ቤት ያስገቡትን ደብዳቤ ሲያጠቃልሉ “ፀረ-ለውጥና ፀረ-ዲሞክራሲ ከሆነው ድርጅት ጋር ለመቀጠል ህሊናዬ ባለመፍቀዱ በገዛ ፈቃዴ ከድርጅቱ አባልነት የለቀኩ መሆኑን እያሳወቅሁ በቅርቡ ያታግለኛል ከምለው  ድርጅት ጋር ተደራጅቼ የራያና የመላ የአገሬ ህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝና ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ እየተደረገ ባለው ርብርብ ለማገዝና ለመታገል እንደምሰራ ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ” ብለዋል።