አቶ ኢሳያስ ዳኛው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ተፈቀደ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 15/2011)የኢትዮ ቴሌኮም የኦፕሬሽን ስራ አስፈጻሚ የነበሩትና በሌብነት የተጠረጠሩት አቶ ኢሳያስ ዳኛው በ50 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ ፍርድ ቤት ፈቀደ።

ፍርድ ቤቱ አቶ ኢሳያስ ዳኛው በ50 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ ፈቅዶላቸዋል።

ፖሊስ በወሳኔው ላይ ይግባኝ ስለመጠየቁ የተገለጸ ነገር የለም።

አቶ ኢሳያስ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት ይፈቱ አይፈቱ የታወቀ ነገር የለም።

መርማሪ ፖሊስ  በኢትዮ-ቴሌኮም ኃላፊ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ኢዲኤም ከተባለው አማካሪ ድርጅት ጋር የስራ ማማከር ውል ያለጨረታ ተዋውለዋል በማለት ወንጅሏቸው ነበር.።

እንደ ፖሊስ ገለጻ በዚህም መሰረት 12 ለሚሆኑ ከኢዲኤም ለመጡ አማካሪዎችና ለድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በሰዓት ከ125-150 ዶላር ያለአግባብ ክፍያ ፈጽመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ለስራ አስኪያጇ ከ500 ሺህ ብር በላይ የቤት ኪራይ እንዲከፈል አድረገዋል፤ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር የተደረገው ውልም ከህግና መመሪያ ውጭ እንዲሻሻል ተደርጓል ብሏል።

በውሉ ላይ እንዲሰሩ የተገለጹ ስራዎች በውሉ መሰረት መሰራታቸው ሳይረጋገጥ 104 ሺህ 495 ዶላር ክፍያ ተፈጽሟል በሚል በሙስና ወንጀል እንደሚጠረጥራቸው ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱም ታውቋል።

በተጠርጣሪው ላይ በተከፈተው አዲስ የምርመራ መዝገብ ላይ ፖሊስ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ መረጃዎችን ለማሳባሰብ የ14 ቀን የምርምራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ አልተፈቀደለትም።

የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው 93 ቀን በእስር ቤት ቆይተው የዋስትና መብታቸውን ሊያስከብሩ ጉዳዩ ባለቀ ሰዓት አዲስ የምርመራ መዝገብ መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን በማስረዳት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር በመመልከትና መዝገቡን መርምሮ በዋለው ችሎት አቶ ኢሳያስ ዳኛው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡና ከሀገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽን እግድ ይጻፍ በማለት ውሳኔ ማሳላፉን ዘገባዎች አመልክተዋል።