አቶ አህመድ አብተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ሆኑ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 23/2011)የፖሊሲ ምርመራና ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አህመድ አብተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ተሾመ።

የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በሆኑት በዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ፊርማ የተሾሙት አቶ አህመድ አብተው ዶክተር ይናገር ደሴን ይተካሉ ተብሏል።

አዲስ ፎርቹን የባንኩን ምንጮች ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ አቶ አህመድ አብተው ከመስከረም 9/2011 ጀምሮ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙ ሲሆን የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት ዶክተር ይናገር ደሴ ስፍራውን ለቀዋል።

ዶክተር ይናገር ደሴ በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ ባንክ ገዢ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በቦርድ ሊቀመንበርነትም ሆነ አባልነት መቀጠል እንደማይችሉም ተመልክቷል።

ዶክተር ይናገር ደሴ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነትን የተረከቡት ከአቶ በረከት ስምኦን ሲሆን አቶ በረከት ስምኦን ለ6 አመታት በቦርድ ሊቀመንበርነት ሰርተዋል።

ከእሳቸው በፊት አቶ አባይ ጸሐዬ የነበሩ ሲሆን ከአቶ አባይ ጸሃዬ በፊት አቶ አሰፋ አብርሃ በቦርድ ሊቀመንበርነት መስራታቸው ይታወሳል።

በሃገሪቱ ትልቁና ቀደምት በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ የሕወሃት ሰዎች በነበራቸው የበላይነት ለኤፈርት በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ሲሰጡና የተበላሸ ብድር በማለት እዳ ሲሰርዙ ቆይተዋል።

75 አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ሺ 288 ቅርንጫፎችና 32ሺ ሰራተኞች እንዳለው ታውቋል።

ባለፈው አመት 11 ቢሊየን ብር እንዳተረፈ የተገለጸ ሲሆን ጠቅላላ ሃብቱ ከ560 ቢሊየን ብር በላይ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ።