አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አሁንም አንዲት ኢትዮጵያ መቀጠል ይገባታል አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 23/2011) ኢትዮጵያ ታላቅ መሪዎች የነበሯት፣ በአለም ላይ የታወቀች ሃገር ስለሆነች አሁንም አንዲት ኢትዮጵያ መቀጠል ይገባታል ሲሉ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ጥሪ አቀረቡ።

እውቁ ፖለቲከኛና የንግድ ሰው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በኢትዮጵያ በተከሰተው ለውጥ መርካታቸውን የገለጹ ሲሆን በእድሜዬ መጨረሻ ይህንን በማየቴም ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በሚኒስትርነት እንዲሁም በአለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ በመሆን ያገለገሉት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በተባበሩት መንግስታት ውስጥም ለረጅም አመታት አገልግለዋል።

በሽግግሩ ዘመን የምክር ቤት አባልና በኋላም የፓርላማ አባላ የነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ንጉስ ሃይለስላሴ ሰዎችን በዘር ማንነታቸው እንደማይመለከቱና መመዘኛቸው ኢትዮጵያዊነት ብቻ እንደነበር ከሬዲዮ ፋና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የንጉሱ መንግስት ሲወገድ የደርግን መንግስት በመቃወም የተንቀሳቀሱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለኦነግ አባልነት ተጠይቀው ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር በተያያዘ ጥያቄውን ሳይቀበሉ መቅረታቸውንም ገልጸዋል።

“ኦነግ ገንዘብ እየለመነ እስከዛሬ ለአላማው በመዋጋቱ እወደዋለሁ ይሔ ውጊያ አላማው ኦሮሞን ገንጥሎ ሌላ ሃገር ለማድረግ ከሆነ አልሰማም ኢትዮጵያውያን በሙሉ አንድ ነን”በማለት በምስረታው ወቅት የቀረበላቸውን የአባልነት ጥያቄ ያልቀጠሉበትንም ምክንያት አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ መሪዎች የነበሯት በአለም ላይ የታወቀች አንድ ሃገር ነች ሲሉም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን/ኦፌዴንን/በመመስረት ከዶክተ መራራ ፓርቲ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ ጋር በማዋሃድ የውህዱን መሪነት ለዶክተር መረራ ጉዲና በመስጠት ራሳቸውን ከፓርቲው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያገለሉት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በቀጣዩ ምርጫ በግል ተወዳድረው ፓርላማ ለመግባት ያላቸውንም ፍላጎት ገልጸዋል።

ዛሬ በመጣው ለውጥ መደሰታቸውን የገለጹት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ መስማት የሚፈልጉትና እንዲቀጥልም የሚመኙት የኢትዮጵያ አንድነት መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬ አራት አመት ገደማ ከደረጃ ላይ በመውደቅ በደረሰባቸው ጉዳት ለአራት አመታት ያህል በአሜሪካና በታይላንድ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አሁን ባለው ሁኔታ ፍጹም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢሕአዴግን በብዙ ነገር ብቀየመውም አብይን ስለሰጠን አመሰግናለሁ ደስ ብሎኝ ነው የምሞተው ሲሉ ገልጸዋል።