አቶ በረከት ስምዖን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2011)አቶ በረከት ስምዖን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ።

አብረዋቸው የተከሰሱት አቶ ታደሰ ካሳ ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ተሰምቷል።

የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው ሁለቱ የቀድሞ የብአዴንና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች  ክሳቸው እንዲቋረጥ  ያቀረቡት መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል።

ተከሳሾቹ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን ማየት ስልጣን የለውም በሚል መከራከራቸውና ጥያቄያቸውም በተመሳሳይ ተቀባይነት ሳይገኝ መቅረቱ ተገልጿል።

ሁለቱ የቀድሞ አመራሮች ከሌላ ሶስተኛ ተከሳሽ ጋር በአራት ክሶች፣በ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ኪሳራ ተጠርጣሪ በመሆን ክስ እንደቀረበባቸው ይታወሳል።

ጥረት ኮርፖሬት የተሰኘውን ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት በአመራርነት ሲሰሩ ድርጅቱን ለኪሳራ ዳርገዋል፣ የሀገር ሀብትን መዝብረዋል፣ ስራቸውን በድለዋል በሚሉ ክሶች ፋይል የተከፈተባቸው የቀድሞ የኢህአዴግና የብአዴን አመራር የሆኑት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተመሰረተብንን ክስ የመመልከት ስልጣን የለውም፣ ወደ ፌደራል ፍርድ ቤት መመራት አለበት የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

ዛሬ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል የተቀመጠው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።

የክልሉ አቃቤ ህግ በበኩሉ ጉዳዩን ለማየትና ብያኔ ለመስጠት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን አለው፣የባከነውና የተመዘበረው ሀብትም የአማራ ክልል ህዝብ በመሆኑ ክሳቸው በክልሉ መታየት አለበት ሲል ተከራክሯል።

አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ሌላው ያቀረቡት ጥያቄ ተፈጸሙ የተባሉት ወንጀሎች የጸረ-ሙስና አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ስለሆነ ልንጠየቅ አይገባም የሚል ነው።

የአማራ ክልል አቃቤ ህግ ጥያቄአቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

ያቀረበው መከራከሪያም የተፈጸመው ወንጀል የጸረ-ሙስና አዋጁ ከጸደቀም በኋላ የቀጠለ ነው በማለት ነው።

ሁለቱ የቀድሞ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ክሳቸው እንዲቋረጥም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

አቃቤህግ በዚህ ጥያቄ ላይ ተቃውሞ በማቅረብ የተፈጸመው ወንጀል በሀገርና ህዝብ ላይ ትልቅ ጉዳት ያስከተለ በመሆኑ ክሱ ቀጥሎ ቅጣት እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ተከራክሯል።

የሁለቱንም ወገኖች መከራከሪያ ያዳመጠው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ በረከት ስምዖን የቀረቡትን ጥያቄዎች ውድቅ አድርጓል።

የክስ መቃወሚያቸውንም ተቀባይነት የለውም ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።

የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው ከሆነ ዛሬ ባህርዳር ላይ የዋለው ችሎት የአቶ በረከት ስምዖንን የእምነት ክህደት ቃል አዳምጧል።

አቶ በረከት የተባለውን ወንጀል አልፈጸምኩም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም ብለዋል።

ከእሳቸው ጋር ሶስተኛው ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛውም የእምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠት ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።

አቶ ታደሰ ካሳ ግን የእምነት ክህደት ቃል አልሰጥም ማለታቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ለግንቦት አምስት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን ችሎት አጠናቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በሌብነትና በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ተይዘው ለቀጣዩ ችሎት እንዲቀርቡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱ ተሰምቷል።

ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በሌሉበት የተከሰሱ ሌሎች አራት ግለሰቦችንም ፖሊስ እጃቸውን ይዞ እንዲያቀርብ በትላትናው ዕለት መታዘዙን ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በትግራይ መቀሌ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የትግራይ ክልል መንግስት አቶ ጌታቸውን አሳልፎ ላለመስጠት መወሰኑ የሚታወስ ነው።