አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከነገ በስቲያ አዲስ አበባ ይገባል

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 11/2011) በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኘው ጀግናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከነገ በስቲያ አዲስ አበባ ይገባል።

በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ የነበረውን አፈና በተለይም በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ግድያ በማውገዝ በአለም አደባባይ የተቃውሞ ድምጹን ላሰማው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከፍተኛ የአቀባበል መርሃ ግብር እንደተዘጋጀለትም ተመልክቷል።

በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ተወዳድሮ 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ያገኘው ጀግናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ቢሊየኖች በቀጥታ በቴሌቪዥንና በአካል በሚከታተሉት አለም አቀፍ መድረክ የተቃውሞ መልዕክቱን እጁን አጣምሮ በማሳየት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው አፈናና ግድያ አለመአቀፍ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል።

በዚህም ሳቢያ በተቃውሞ ለውድድር እንደወጣ በዛው የቀረውና ላለፉት ሁለት አመታት ያህል ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የፊታችን እሁድ ከአሜሪካ አዲስ አበባ ይገባል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማህበር እንዲሁም የአዲስ አበባ መስተዳድር የአቀባበል ፕሮግራሙን በጋራ ማዘጋጀታቸው ተመልክቷል።

ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ አዲስ አበባ ስታዲየም በሚካሄደው የአቀባበል መርሃ ግብር ጀግናው አትሌት ንግግር ያደርጋልም ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሮግራሙ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ስታዴም እንደሆነም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ያገኘው በነሐሴ ወር 2008 ሲሆን በኢትዮጵያ የሚኖሩት ባለቤቱና ልጆቹ በየካቲት ወር 2009 ስደተኛውን አትሌት ተቀላቅለዋል።

ከሁለት አመታት ስደት በኋላም የፊታችን እሁድ መስከረም 13/2011 ጀግናው አትሌት አዲስ አበባ ሲደርስ እጅግ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት ይጠበቃል።