አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ትኩረት እንድትሰጥ ጠየቀ

ኢሳት (የካቲት 9: 2009)

በነሃሴ 2009 በብራዚል ሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን የብር ሜዳሊያ ያሸነፈው ጀግናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ትኩረት እንድትሰጥ ጠየቀ። በቢሊዮኖች በሚከታተሉት መድረክ ተቃውሞውን ካቀረበ ከስድስት ወራት በኋላ በዚሁ ሳምንት መጀመሪያም ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ጋር በአሜሪካ ተገናኘ።

በአለም አቀፍ የኦሎምፒክ መድረክ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የሰብዓዊ መብት ረገጣ በመቃወም የአለም ሚዲያ መነጋገሪያ የነበረው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ,  ዩኤስ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ትኩረት እንድትሰጥ ጠይቋል። ከቤተሰቦቹ ጋር በመገናኘቱም አሜሪካንን አመሰግኗል።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ባለቤቱ ኢፍቱ ሙሊሳና ሁለት ልጆቹ አሜሪካን መግባታቸውን ተከትሎ፣ በአሶሼይትድ ፕሬስ በኩል ባስተላለፈው መልዕክት፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ላይ አሜሪካ ትኩረት እንድታደርግና ድጋፉም ይህንኑ መሰረት ያደረገ እንዲሆን ጠይቋል።

በዩኤስ አሜሪካ ልዩ የስደተኛ ቪዛ በአሜሪካ የሚገኘው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ ከቤተሰቡ ጋር እንዲገናኝ ዩ ኤስ አሜሪካ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል።

ቤተሰቦቹን በፍሎሪዳ ሚያሚ የተቀበለው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ ወደ ጊዜያዊ መኖሪያው አሪዞና ቤተሰቦቹን ይዞ ተጉዟል።