አርቲስት ታማኝ በየነ በጎንደር ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት

አርቲስት ታማኝ በየነ በጎንደር ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ/ም ) ከሃያ ሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ የተመለሰው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና አርቲስት ታማኝ በየነ በዛሬው እለት በጎንደር ከተማ በመገኘት ከሚወዱት አድናቂዎቹ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቷል።
ታማኝን በየነና ባለቤቱን አርቲስት ፋንቲሽ በቀለን ለመቀበል የከተማ ነዋሪዎች፣ የክልሉ ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በመገኘት ደማቅ የክብር አቀባበል አደርገውለታል።
አርቲስት ታማኝ በየነ አገዛዙ በመላው ኢትዮጵያ ስለፈጸማቸው የመብት ጥሰቶች በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በማንነቱ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መጠነ ሰፊ መሆናቸውን ጠቅሷል። ሕዝቡ ከደረሰበት የጅምላ የዘር ፍጅትና ሰቆቃ ለመከላከል ራሱን አደራጅቶ መታገሉን እንደማይቃወምም አስታውቋል። ነገርግን ብቸኛው መዳኛ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን የተናገረው ታማኝ በየነ ”እኔ ማንንም እየለመንኩ ኢትዮጵያዊ አላደርገውም። ኢትዮጵያዊነት በራሱ ክብር ነው፣ ኢትዮጵያዊነት ያኮራል፣ ቢላል ኢትዮጵያዊ ነው። መከራ ሲመጣ መስቀላቸውን የሚያስቀምጡበት ዘመን በታጣ ወቅት እምቢ ያሉት አቡነ ጴጥሮስ ናቸው። ኢትዮጵያዊነት አይደክምም። ” ብሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸሙት ጭፍጨፋዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ በመቀጠል ተጠያቂ የሆኑን አቶ በረከት ስምዖንን አስመልክቶም ”የብአዴን አመራር የሆኑት አቶ በረከት ጎንደር ነው የተወለዱት። ጎንደር ማንነታቸውን ጠይቆ አያውቅም። ጥቅማችን አስጠብቁ እንጅ ከኤርትራ መጡ አላላቸውም። በአመራርነት ግን ወደቁ። የተለያየ ቋንቋ ስላለ ልዩነታችን የጥላቻ አናድርገው።” ሲል በአምንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ጨምሮ የጅምላ የጎዳና ላይ ፍትሕ እንዲቀር አስጠንቅቋል።
ታማኝ በየነ በየነ በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በትውልድ ከተማው ራስ ጋይንትና ጎንደር ከተሞች በመገኘት ኢትዮጵያዊያን በጋር ለሰብዓዊ መብትና ለህግ ልእልና መከበር በተቋም ደረጃ በጋራ ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።