አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ሊሾሙ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 20/2011) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ተጠሪዎች፣ የአምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ሹመት እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ሹመቱ ከፖለቲካ ታማኝነት ይልቅ እውቀት፣ ልምድና እንዲሁም በህብተረሰቡ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች እንደሚገኙበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዓለም  በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት አዳዲሶቹ አምባሳደሮች በተልዕኳቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተደረገ ማሻሻያ በጎረቤት ሀገራት የሚሾሙ አምባሳደሮች ላይ በተለየ አሰራር ለውጥ እንደሚኖር ገልጸዋል።

59 አምባሳደሮችና 11 የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጄነራል ዳይሬክተሮች ሹመት ይሰጣል።

ካሉት 412 ዲፕሎማቶች መካከልም ከግማሽ የሚበልጡት እንዲዘዋወሩ ተደርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተግባራዊ እያደረገው ባለው የማሻሻያ ርምጃ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የሚሰሩ ዲፕሎማቶች ላይ አዲስ አሰራር መከተሉን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት በአዲሱ አሰራር መሰረት የአምባሳደሮችና የዲፕሎማቶች ሹመት በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን ይሆናል።

እስካሁን እንደነበረው የኤምባሲና የኢትዮጵያውያን ግንኙነት የሻከረ ሳይሆን ኢትዮጵያውያኑ ሲደሰቱም ሲያዝኑም እንደቤታቸው የሚመለከቱት እንዲሆን ተደርጎ የሚዋቀር ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ አቶ መለስ አለም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያከናወነ ባለው የማሻሻያ ስራ የሃገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር እና ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ተቋም እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለኢሳት የገልጹት።

ሹመትና ምደባ የሚሰጣቸው አምባሳደሮች፡ የኦንስላ ጄነራሎችና በአጠቃላይም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ዲፕሎማቶች የተመረጡበት መመዘኛዎች እንደከዚህ ቀደሙ ፖለቲካዊ ታማኝነት ብቻ ታይቶ እንደማይሆን ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዕለም ይናገራሉ።

ዕውቀትና ክህሎትን መሰረት ያደረገ ፡ ከውጭ ምሁራንና የአካዳሚክ ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦችን እንዲያካትት ተደርጓል ብለዋል።

የሀገሩንና የህዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም እንዲሆንም የተደረገበት ሹመትና ምደባ መሆኑን ነው ቃል አቀባይ ዓለም መለስ የሚገልጹት

በአዲሱ የማሻሻያ ስራ ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት መደረጉንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውጥረት አልባ የሆነ ግንኙነት ከጎረቤት ሃገራት ጋር እንዲኖራት ስለምትፈልግ ብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው አንጋፋ ዲፕሎማቶችን በጎረቤት ሃገራት እንዲመደቡ መደረጉንም አቶ መለስ ዓለም ለኢሳት ገልጸዋል።

በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች የሚሰማሩ ዲፕሎማቶች ስም ዝርዝር በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ገልጸዋል።