አልማ ለገቢ ማስገኛ በሚል ያስገነባው ማተሚያ ቤት ከጥቅም ውጪ መሆኑ ተነገረ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 5/2009) የአማራ ልማት ማህበር/አልማ/ለገቢ ማስገኛ በሚል ያስገነባው ማተሚያ ቤት የህትመት ማሽኑን ሊያስገባ ባለመቻሉ 24 ሚሊየን ብር የወጣበት ግንባታ ከጥቅም ውጪ መሆኑ ተነገረ።
ባልተጠና የግንባታ ዲዛይን የተሰራው ማተሚያ ቤት ከጥቅም ውጪ ከሆነ በኋላ በሌላ ቦታ ግንባታ ለማከናወን የተገዛው ከ900 በላይ ከረጢት ሲሚንቶም ተበላሽቶ መጣሉ ተነግሯል።
በአያያዝ ችግር እንዲወገድ የተደረገው የአማራ ልማት ማህበር/አልማ/ ከ900 በላይ ከረጢት ሲሚንቶ ከ324 ሺ ብር በላይ ወጭ የተደረገበትና የባከነ ነው።
ከአመታት በፊት በአቶ ህላዊ ዮሴፍ ሲመራ የነበረው የአልማ ጽህፈር ቤት በከፍተኛ የኦዲት ጉድለት በመጠርጠሩ ህንጻው ሙሉ በሙሉ እንዲቃጠል ተደርጎ ማንም ሳይጠየቅ መቅረቱ ይታወሳል።
የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/በቴሌቶን አማካኝነት በገቢ ማሰባሰብ ከሕዝብ አግኝቻለሁ ያለውን ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ በምን ስራ ላይ እንዳዋለው በዝርዝር ሳይታወቅ ተንጠልጥሎ የቆየ ጉዳይ ነው።
የማህበሩ ወጪና ገቢ ታውቆ የኦዲት ሪፖርት ለሕዝብ ግልጽ ተደርጎ አያውቅም።አሁን ያገኘንው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ የአልማ ጽህፈት ቤት ገቢ ለማግኘት በሚል ያሰራው የአባይ ማተሚያ ቤት ሕንጻ ትክክለኛ ባልሆነ ዲዛይን ሳቢያ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።
ከ24 ሚሊየን ብር በላይ የወጣበት ይህው ህንጻ የሕትመት ማሽኖችን ሊያስገባ አልቻለም በሚል ያለአገልግሎት በቁሙ ቀርቷል ነው የተባለው።
ይባስ ብሎ ደግሞ በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 11 ዘንዝልማ መውጫ ላይ ሌላ የማተሚያ ቤት ሕንጻ እንሰራለን በሚል ከ900 በላይ ከረጢት የደርባን ሲሚንቶ ከ324 ሺ ብር በላይ ወጪ ቢገዛም በአያያዝ ችግር መበላሸቱን የኢሳት ምንጮች በቪዲዮ አስደግፈው ጠቁመዋል።
የአባይ ማተሚያ ቤት መጀመሪያ ሲገነባ የአልማ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሰለሞን ታደሰና የማህበሩ የገቢ ማስገኛ ክፍል ሃላፊ የነበረው አቶ ታደሰ ጊዮን ድርጅቱን ቢለቁም ከብክነቱና በህንጻው ስም ለተበላው 24 ሚሊየን ብር ተጣያቂ መሆናቸው ተመልክቷል።
የአካባቢው ምንጮች የተበላሸና ሲሚንቶም ከቀበሌ 11 ወደ ቀበሌ 07 ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ፊት ለፊት ባለ ግቢ እንዲከማች ተደርጓል።
በአማራ ልማት ማህበር/አልማ/ከቴሌቶን ገቢ ለክልሉ ጤና ጣቢያዎች አምቡላንሶች ተገዝተው ብዙዎቹ ያለአገልግሎት ቆመው ሲቀሩ ተጠያቂ የተደረገ አካል የለም።
ከአመታት በፊትም አልማ በአቶ ህላዊ ዮሴፍ ሲመራ በነበረበት ጊዜ ከፍተኛ የኦዲት ጉድለት እንዳለ በመጠርጠሩ ጽህፈት ቤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቃጠል ተደርጎ ምክንያቱ ለሕዝብ ሳይገለጽ ጉዳዩ ተሸፋፍኖ ቀርቷል።
በአሁኑ ጊዜ የአማራ ልማት ማህበር በዋና ዳይሬክተር በወይዘሮ ብስራት ጠናጋሻው ቢመራም ሴትዬዋ መኖሪያቸው አዲስ አበባ በመሆኑ በሳምንት 2 ጊዜና 3 ጊዜ በአውሮፕላን ባህርዳር ስለሚመላለሱ የትራንስፖርት ወጪያቸው ብቻ ቀላል የማይባል ብክነት መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
እናም የባህርዳር ምንጮቻችን የአማራ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ይህን እያየ ዝም ማለቱ እስገራሚ ነው ባይ ናቸው።