አለማቀፍ የኡንዲስትሪያል ህብረት የኢትዮጵያ ሰራተኞች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ዘመቻ ጀመረ

አለማቀፍ የኡንዲስትሪያል ህብረት የኢትዮጵያ ሰራተኞች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ዘመቻ ጀመረ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 08 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢትዮጵያ ውስጥ በጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዱስትሪዎች የሚሰሩ ሰራተኞች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ለማድረግ ኢንዳስትራያል ግሎባል ዩኒየን የተባለው የሰራተኞች ማህበር ዘመቻ ጀምሯል። በእነዚህ እንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን በወር 20 ዶላር አካባቢ የሚከፈላቸው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሰራተኞቹ የመጨረሻ ክፍያቸው በወር 121 ዶላር ወይም 3 ሺ 373 ብር እንዲሆን ለማድረግ ዘመቻ ጀምሯል።
ዘመቻው በቦሌ ለሚ ፣ ሃዋሳና መቀሌ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማዕከል አድርጓል። 90 በመቶ የሚሆኑ በፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ሴቶች የምግብ፣ የትራንስፖርት እና የቤት ወጪያቸውን ለመሸፈን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር አይችሉም። እነሱ የሚያመርቱዋቸው ምርቶች በአውሮፓ፣ አሜሪካ እና እስያ ገበያዎች በውድ እየተሸጡ ባለሃብቶቹ ከፍተኛ ገቢ ያገኙባቸዋል። የሰራተኞችን ዝቅተኛ የደሞዝ ጣሪያ ለማሻሻል የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበርና የአለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ከገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ጀስት ስታይል ዘግቧል።
በቦሌ ለሚ እንዱስትሪ ፓርክ የሚሰሩ ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለመጠየቅ ትናንት የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ በፖሊሶች ሲዋከቡ አርፍደዋል።