ነዋሪነቱ በስዊትዘርላንድ ሲዮን ከተማ የነበረውና በበርካታ ሀገራዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ አቶ መኳንንት መታፈሪያ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ሰኔ ፪ ( ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ መኳንንት መታፈሪያ የሀገሩንና የወገኑን ጉዳይ እንደግል ጉዳዩ በመወሰድ ለኢትዮጵያዊያን የመብት ትግል ያለመታከት የዜግነት ድርሻውን ሲወጣ የኖረ ጎልማሳ ነበር።
አቶ መኳንንት ከሰብአዊና ማህበራዊ ትጋቶቹ በተጨማሪ በሚኖርበት ከተማ የኢሳትን ቻፕተር በመመስረት ድጋፍ በማስተባበርና እራሱም በመደገፍ ሊረሳ የማይችል ተግባር ሲፈጽም እንደነበረ የስዊትዘርላንድ ኢሳት ድጋፍ ኮሚቴ ለኢሳት በላከው የሀዘን መግለጫ ጠቅሷል።
የአቶ መኳንንት የቀብር ስነ ስርዓት የሚፈጸመው የፊታቸን ሰኞ በ15 ሰዓት ሲዮን ከተማ ሩደ ሎሄ 1950 ወዳጅ፣ ዘመድ ጓደኞች በተገኙበት እንደሚፈጸም ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። አቶ መኳንንት መታፈሪያ የ47 ዓመት ጎልማሳና የ11 ዓመት ሴት ልጅ አባት ነበር። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ራድዮ በአቶ መኳንንት መታፈሪያ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹና ለስዊትዘርላንድ ኢሳት ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል።