ቴዲ ማንጁስ ከቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ጋር ግንኙነት ነበረው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 26/2011)በሶማሌ በተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠረው ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ከቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ጋር ግንኙነት እንደነበረው ተገለጸ።

በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 26 እስከ 30/2010 ዓ.ም. ተፈጥሮ በነበረው  ግጭት ተጠርጥሮ የታሰረው አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋርም  ግንኙነት እንደነበረው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ገልጿል፡፡

በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ ግድያ፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃትና ማፈናቀል ከሐምሌ 26 እስከ 30/2010 ዓ.ም. ተፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም።

በዚሁም የሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎና ንብረት ዘረፋ መፈጸሙም ነው የሚታወሰው።

እናም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ)፣ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከነበሩት አቶ አብዲ መሐመድና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ለፍርድ ቤት ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ጥቅምት 23/2011 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው ግለሰቡ በክልሉ ታዋቂ ባለሀብት ነው፡፡

ግለሰቡ በፌስቡክና በተለያዩ መንገዶች ባደረገው ቅስቀሳም በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ እንዲባባስ አድርጓል ተብሏል፡፡

አሁን በእስር ላይ ከሚገኙት የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንትና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋርም ግንኙነት እንደነበረው ማስረጃዎችን ማሰባሰሰቡንም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል ፡፡

ባለሃብቱ አሁን በሥራ ላይ ከሚገኙ የቀድሞ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት አለው ብሎ ስለሚያስብም ምስክሮችን ሊያባብል፣ ሊያስጠፋ፣ ሊያስፈራራ፣ ሰነዶችንም ሊያጠፋ ስለሚችል የጠየቀውን ዋስትና እንደሚቃወም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በተጠርጣሪው ላይ በተሰጠው የ14 ተጨማሪ ቀናት ቀጠሮ የሦስት ምስክሮችን ቃል መስማቱን፣ የግለሰቡን የተከሳሽነት ቃል መቀበሉን፣ የጣት አሻራ ለፎረንሲክ ምርመራ መስጠቱን፣ የወንጀል ድርጊት እንዲፈጸም ሲነጋገርባቸው የነበሩ ሁለት ሞባይል ስልኮች ለቴክኒክ ምርመራ መስጠቱን ፖሊስ ለፍርድቤቱ አስረድቷል።

ግለሰቡ ባነሳሳው ሁከትና ብጥብጥ የሞቱ በርካታ ሰዎች በጅምላ ከተቀበሩበት አስከሬናቸው ወጥቶ እንዲመረመር ሰጥቶ ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑንም ፖሊስ  ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ሌሎች ግብረ አበሮችን መያዝ፣ የቀሩ ምስክሮችን ቃል መውሰድ፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት መቀበል፣ የተጎጂዎችን ምርመራ ውጤት ማሰባሰብ፣ ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጪ ከተደረገው ገንዘብ ግለሰቡ ተቋዳሽ በመሆኑም ወጪ የተደረገበትን ሰነድ ማስተርጎም ስለሚቀረው፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ ) ጠበቃ አቶ ዳግም ተሾመ  ባቀረቡት መቃወሚያ፣ ደንበኛቸው የተጠረጠረበት ጉዳይ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ለፍርድ ቢቱ ተናግረዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ከታሰረ አንድ ወር እንዳለፈውና በጅግጅጋ ቃሉን እንደሰጠም ነው የገለጹት።

ግብረ አበሮችን መያዝ የፖሊስ ሥራ በመሆኑ ደንበኛቸውን በማቆያ ቤት የሚያስቆይ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ለቀሪ ምርመራ ፖሊስ የጠየቀው ጊዜ ተገቢ መሆኑን በማመን የተጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) በማህበራዊ ሚዲያ የህወሃትን አገዛዝ በመደገፍ የጥላቻ ጽሁፍ ሲያዛምት እንደነበር አይዘነጋም።