ቱባቱባ የቀድሞ ባለስልጣናትን ወደ አንድ ቦታ መሰብሰብ ይገባል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 05/2011) በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስርዓት አልበኝነት መልክ ለማስያዝ ቱባቱባ የቀድሞ ባለስልጣናቱን ወደ አንድ ቦታ መሰብሰብ እንደሚገባ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አሳሰቡ።

የትግራይ ህዝብም በውስጡ የበቀሉትንአረሞች እየሰማ የነርሱ መሸሸጊያ ሊሆን አይገባም ያሉት ፕሮፌሰርር መስፍን ወልደማርያም ሌላውም ህዝብ የትግራይን ህዝብ ከህዉሃትለይቶ እንዲመለከት ጥሪ አቅርበዋል።

እነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚሰብኩት ፍቅር፣ ሰላምና ይቅር ባይነት በህጋዊ ሰይፍ ካልታገዙ እነሱንም ሆነ ህዝቡን ወደ መከራ የሚያስገባ በመሆኑ አድሎ የሌለበት ህጋዊ ርምጃ መውሰድ የግድ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተናግረዋል።

በዩ ኤስ አሜሪካ ለአንድ ወር ያህል ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ በወያኔ ሲያጠነጥን የነበረውን የጥላቻ ጉንጉን በአንድ ጊዜ ለመፍታት ሞክረዋል በሚል ስለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ለለውጡ መሪዎች የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም- የኢትዮጵያም ህዝብ መንገዱን መከተልና የራሱን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ትልልቅ ውሳኔዎችን ከመወሰናቸው በፊት ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቁት ሰዎችን ቢያማክሩ ይሻላል በሚል ለለውጡ መሪዎች ምክር የለገሱት አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሃገሪቱ መረጋጋት እንዲመጣ ከፍቅርና ሰላም ስብከት ባሻገር ከህግ ጋር ሰይፍ ጭምር ያስፈልጋል ብለዋል።

ከስልጣን የወረዱትን ዋና ዋና ባለስልጣናት ሰብስቦ ማስቀመጡም የግድ ነው ሲሉም አሳስበዋል።

ከሁለት ሺህ አመት በላይ ፍቅርና ይቅር ባይነት የተሰበከበት ሃገር ውስጥ የፖለቲካ መሪዎች ይህንኑ ብቻ እየሰበኩ ህጋዊ ሰይፍ ሳያነሱ ሰላምን ማረጋገጥ አይችሉም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በዝምታቸው ከቀጠሉ ለእነርሱም አደጋ ለኢትዮጵያም መከራ ይተርፋል ሲሉ አሳስበዋል።

የለውጡ መሪዎች እና ዶክተር አብይ አህመድ የሚቆጡበትና ወደ ርምጃ የሚሄዱበት ቀን እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እኔ የማዝነው ሁሌም በመከራ ውስጥ ለሚያልፈው የትግራይ ህዝብ ነው ሲሉ የህውሃት ጦስ ለህዝቡ እንዳይተርፍ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ህወሃት ከኤርትራ ህዝብ እንዲሁም ከጎንደር ከአፋር እና ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጠላትነት ከፈጠረ እና ከተከበበ በኋላ የህዉሃት መሪዎች የትግራይን ህዝብ ማግደው ለማንሰራራት ማሰባቸው ዕውነት የመገንዘብ ችሎታ እንደሌላቸው ያሳያል ሲሉ ተችተዋል።

         በትግራይ ውስጥ የበቀሉትን እነዚህን አረሞች ለመንቀል የትግራይን ህዝብ በማያሳዝን መልኩ መሰራት አለበት ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የትግራይን ህዝብ ከህዉሃት ለይቶ መመልከቱ ከሌላው ህዝብ ይጠበቃል ሲሉም መክረዋል።