በጠምባሮ ዞን 10 መምህራን ቆስለው ሆስፒታል ሲገቡ በርካቶች ደግሞ ታሰሩ

በጠምባሮ ዞን 10 መምህራን ቆስለው ሆስፒታል ሲገቡ በርካቶች ደግሞ ታሰሩ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 07 ቀን 2010 ዓ/ም) በደቡብ ክልል በከምባታ ጠምባሮ ዞን የሚገኙ መምህራን ለልማት በሚል ያለፍላጎታቸው ከወር ደሞዛቸው ላይ መቆረጡን በመቃወማቸው 10 መምህራን በፖሊሶች ድብደባ ተፈጽሞባቸው ሆስፒታል ሲገቡ፣ 20 መምህራን ደግሞ የለምንም ጥያቄ ተስረዋል።
በዚህም የተነሳ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ትምህርት ተቋርጧል። መምህራኑ ከዚህ በፊት ለአባይ ግድብ በሚል የወር ደሞዛቸው እንደተቆረጠባቸው ገልጸው በድጋሜ ለከተማ ልማት በሚል እንዲቆረጥባቸው የተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበሉት አስታውቀው ነበር። ይሁን እንጅ ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ መምህራኑ ገንዘብ ከደሞዛቸው ላይ መቆረጡን በማየታቸው አቤቱታቸውን ለክልል ባለስልጣናት አቅርበዋል። የክልሉ ባለስልጣናት ከመምህራኑ ላይ የተቆረጠው ገንዘብ እንዲመለስ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ የዞኑና የወረዳው ባለስልጣናት ግን ትዕዛዙን እንደማይቀበሉት በማስታወቅ ከሚያዚያ ወር ክፍያ ላይ ገንዘብ ቆርጠዋል አስቀርተዋል። መምህራኑ በተወካዮቻቸው አማካኝነት በድጋሜ ለወረዳው አስተዳዳሪ ጥያቄ ሲያቀርቡ ተደብድበው እስር ቤት እንዲገቡ መደረጋቸውን፣ ካለፈው አርብ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ታስረው እንደሚገኙ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ መምህራን ተናግረዋል።
በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው መምህራን ህክምና እያገኙ መሆኑን የገለጹት መምህራን፣ በተወሰደው እርምጃ በመምህራኑና በተማሪዎች ላይ የሞራል ውድቀት እንዳሳደረ ተናግረዋል።