በጎንደር ጀግኖች ሲታሰቡ ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 5/2010) በሐምሌ አምስት የተሰዉ ጀግኖችን በማሰብ በጎንደር ከተማ የሻማ ማብራትና የውይይት  ፕሮግራም ተካሄደ።

ሐምሌ አምስት 2008 ዓመተምህረት የህወሃት ታጣቂዎች የወልቃይ የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባል ኮለኔል ደመቀ ዘውዴን ለማፈን ያደረጉት ሙከራ የተቀለበሰበት 2ኛ ዓመት መታሰቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ የጎንደር ነዋሪዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት መካሄዱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በእለቱም ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ በትግሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ግለሰቦች ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ ሳይመለስ መቼም ከመስመራችን ዝንፍ አንልም ብለዋል ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ።

ሀምሌ 5/2008 ዓም። የዛሬ ሁለት ዓመት። ዕለቱ ማክሰኞ ነው።

የህወሀት ታጣቂዎች ወንዝ ተሻግረው ጎንደር ከተማ ከገቡ ቀናት አልፏቸዋል።

የመጡት የወላቃይ የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባል የሆኑትንና በትግሉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉትን ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን አፍኖ ወደትግራይ ለመውሰድ ነበር።

ለቀናት ሁኔታዎችን ካጠኑ በኋላ ቀን ቆርጠው ወደ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ መኖሪያ ቤት ያመራሉ። ሀምሌ 5 – ማክሰኞ።

የህወሀት ታጣቂዎች ጎንደር ገብተው ሆቴል ይዘው የአፈና ዘመቻቸውን ሊፈጽሙ ሲዘጋጁ መረጃው የደረሰቸው የነጻነት ሃይሎች አፈናውን ለመመከት በተጠንቀቅ ይጠብቁ ነበር።

ቀኑ ደርሶ የህወሀት ታጣቂዎች ወደ ኮለኔል ደመቀ መኖሪያ ቤት አምርተዋል።

በዙሪያው በዝግጅት ላይ የነበሩት የነጻነት ሃይሎች አፈናውን ለመቀልበስ ርምጃ መውሰድ ጀምሩ።

ከኮለኔሉ መኖሪያ ቤት አጥር ዘለው ሊገቡ የነበሩ ሁለት የህወሃት ታጣቂዎች ወደ ውስጥ ከመዝለላቸው በፊት ተመተው ወደቁ።

ሌሎች ታጣቂዎች የኮለኔሉ መኖሪያ ቤት ከመድረሳቸው በፊት በነጻነት ሃይሎች ርምጃ ተወሰደባቸው። ይህን ተከትሎም በተፈጠር ግጭት ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችም ተገደሉ።

ሃምሌ 5 የአማራ ህዝብ ትግል ከነበረበት ጉዞ በፍጥነት ወደ አጥቂነት የተሸጋገረበት ቀን እንደሆነም ይነገራል።

የወልቃይት የአማራ ማንነት የወልቃይት ተወላጆች ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የአማራና የመላው ነጻነት ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ወደ መሆን የተቀየረበት ዕለት መሆኑም ይገለጻል።

ዛሬ ይህ ዕለት ሁለተኛ ዓመቱ በድምቀት ተዘክሯል። በጎንደር ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተገኙበት በሻማ ማብራትና በውይይት ሀምሌ አምስት ተዘክሯል።

በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ያሸበረቀው የመታሰቢያ ፕሮግራሙ በዕለቱ የነበረውን ተጋድሎና ከዚያን ወዲህ የአማራው ህዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያሳዩ የተለያዩ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ፣ አርበኛ ደጀኔ ማሩ፣ ታጋይ ንግስት ይርጋና ሌሎች የሀምሌ አምስቱ ተጋድሎ የፈጠራቸው ጀግኖች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ጥያቄ ሳይመለስ መቼም ከመስመራችን ዝንፍ አንልም ማለታቸውም ተገልጿል።

አርበኛ ደጀኔም የተከፈለውን መስዋዕትነት የተመለከተ ንግግር ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከፕሮግራሙ በኋላ ወደ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ መኖሪያ ቤት በሰልፍ ያመራው የመታሰቢያ ፕሮግራሙ ታዳሚ ለህወሃት አገዛዝ ያለውን ተቃውሞ ማሰማቱ ታውቋል።