በጅቡቲ ሁለት ጀልባዎች ተገልብጠው 28 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2011)በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ስደተኞችን የጫኑ ሁለት ጀልባዎች ተገልብጠው 28 ሰዎች ሲሞቱ ከ100 የሚበልጡት የገቡበት አለመታወቁን አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገለጸ።

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዓለም አቀፉን የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤምን ጠቅሶ እንደዘገበው አደጋው የደረሰው ጀልባዎቹ ጉዞ በጀመሩ በ30 ደቂቃ ውስጥ በገጠማቸው ወጀብ ሲሆን ጎዶሪያ በተባለው የጅቡቲ ግዛት አደጋው መከሰቱም ተመልክቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎችን ጥቆማ መነሻ በማድረግ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ባደረጉት አሰሳ ሁለት ሰዎችን በህይወት ያገኙ ሲሆን የሶስት ሴቶችንና የሁለት ወንዶችን አስከሬንም ማውጣታቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

ዛሬ በቀጠለው ፍለጋም ተጨማሪ የ23 ሟቾች አስከሬን መገኘቱ ተዘግቧል።

ከአደጋው ከተረፉት አንዱ በሰጠው መረጃ በመርከቡ 130 ያህል ሰዎች የተሳፈሩ ሲሆን የባህር ዳርቻ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በሁለት ጀልባ በሕይወት የተረፉትን ለመታደግና የሞቱትንም ለማንሳት በፍለጋ ስራቸውን ቀጥለዋል።

በጀልባዎቹ ላይ የነበሩት የሞቱትም ሆነ የተረፉት እንዲሁም የደረሱበት ያልታወቀው ስደተኞች የየት ሃገር ዜጎች እንደሆኑ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።