በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ብሔር ተኮር የሆነ ጥቃት እየተፈጸመ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2011) በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ብሔር ተኮር የሆነ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ ተገለጸ።

አንዳንድ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እንደሚሉት በየጊዜው ከሚደርስባቸው ጥቃት ጋር በተያያዘ 700 የሚሆኑ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን ለቀው ከወጡ ሁለት ወራት ተቆጥሯል።

በግቢው የቀሩት ተማሪዎች ላይም በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ተማሪዎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱን ያደርሳሉ የተባሉት አንዳንድ ተማሪዎች ዶርም ውስጥ ገጀራን የመሳሰሉ መሳሪያዎች ቢገኙም አስተዳደሩ ግን እነዚህ ተማሪዎች ላይ ርምጃ ሊወስድ አልፈለገም ብለዋል።

ኢሳት ያነጋገረው አንድ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በተደጋጋሚም እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ለዩኒቨርስቲው አስተዳደር አቤት ቢሉም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል አለማግኘታቸውን ገልጿል።

ኢሳት የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ አስተዳደርንና የተማሪዎች አገልግሎት ክፍልን ለማነጋጋር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ብሄር ተኮር በሆነው ጥቃት የተነሳ መማር አልቻልንም የሚሉት ተማሪዎች አንዲት የዩኒቨርሲቲው ተማሪ በለበሰችው ቲሸርት ምክንትያት በመንጋ ሆነው ድብደባ እንደፈጸሙባት ኢሳት ያነጋገርው ተማሪ ገልጿል።

አሁንም የዩኒቨርስቲው አስተዳደርም ሆነ የሚመለከተው አካል በዩኒቨርስቲው እየተፈጸመ ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃት እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉት ተማሪዎች በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን ጥያቄ ተመልክቶ አስቸኳይ ምላሽም እንዲሰጣቸው አመልክተዋል።