በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የ45 ሰዎች ሕይወት አለፈ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/2010)

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ርዕሰ መዲና ኪንሻሳ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ45 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

በአደጋው ከሞቱት ውስጥ አምስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል።

ከአፍሪካ ከተሞች በሕዝብ ብዛት በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውና 12 ሚሊየን ያህል ሕዝብ የሚኖርባት የኮንጎዋ ርዕሰ መዲና ኪንሻሳ ነዋሪዎች የአደጋው ሰለባ የሆኑት ለ5 ቀናት ያህል ሳያቋርጥ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ እንደሆነም ታውቋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ እስከ እሁድ ሳያቋርጥ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጉርፍ በከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች ቤቶችን እየጠረገ ሲወስድ ከደረሰው አደጋ ባሻገር ጎርፉ ባስከተለው የአፈር መንሸራተት ብዙዎች ሰለባ መሆናቸውም ተመልክቷል።

አልጀዚራ የሰለባዎቹ የቀብር ስነስርአት ላይ ያነጋገረው ባዲባንጋ የተባለ የኪንሻሳ ከተማ ነዋሪ በእህቱ ላይ የደረሰው አደጋ የከፋ እንደነበር ገልጿል።

“እጅግ በጣም አዝነናል እህቴ በዝናቡ ምክንያት አምስት ልጆቿን አጥታለች” ሲልም በቤተሰቡ ላይ የደረሰውን ጉዳት ዘርዝሯል።

በ24 ሰአት ውስጥ 182 ሚሊሜትር የተመዘገበበት ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ በቀጥታ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ በከተማዋ የተስፋፋው የኮሌራ በሽታ ስጋትን ደቅኗል።

ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን እንዳስታወቀው ለወትሮው በሳምንት 20 ያህል የኮሌራ ህሙማን ይመዘገቡባት የነበረችው ኪንሻሳ ከጎርፉ አደጋ በኋላ የህሙማኑ ቁጥር ወደ 100 ከፍ ብሏል።

በአሁኑ ወቅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ርዕሰ መዲና 450 ያህል የኮሌራ ተጠቂዎች ተመዝግበዋል።

45 ሰዎች ለሞቱበትና 5ሺ ያህል ሰዎችን ቤት አልባ ያደረገው አደጋን ተከትሎ በሀገሪቱ የሁለት ቀናት የሀዘን ቀን ታውጇል።

የሀገሪቱ መንግስት ለአደጋው ህገወጥ ሰፋሪዎችን ተጠያቂ አድርጓል።

በህገወጥ ግንባታዎች የውሃ መውረጃ ቱቦዎች መዘጋታቸው ለጎርፉ አደጋ ምክንያት ሆኗል ሲልም የተጠያቂነቱን ምክንያት አብራርቷል።