በደብረታቦር ከግብርና ከአስተዳደር በደል ጋር ተያይዞ የተጀመረው አድማ መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 3/2009) በደብረታቦር ከግብርና ከአስተዳደር በደል ጋር ተያይዞ የተጀመረው አድማ ለ3ኛ ቀን ተጠናክሮ መቀጠሉ ተሰማ።
በከተማዋ ሁሉም የንግድ መደብሮች ዝግ ሲሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ እንደቆመ ነው።
የአካባቢው ካድሬዎችና ፖሊሶች የተሽከርካሪዎችን ሰሌዳ በግዳጅ እየፈቱ መሆናቸው ተነግሯል።
ሕዝቡ ግን የንግድ መደብሮችን በሚከፍቱና ተሽከርካሪ በሚያንቀሳቅሱት ላይ እርምጃ እንወስዳለን በማለት በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
በደብረታቦር ለ3ኛ ቀን የቀጠለው አድማ መረር ያለና ጠንካራ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የሕወሃት/ብአዴን ካድሬዎች ቤት ለቤት እያስፈራሩና ታሽጓል የሚል ወረቀት እየለጠፉ ለማስከፈት ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም ነው የተባለው።
በከተምዋ ከ5 በመቶ በላይ ባጃጆች ስራ ማቆማቸው ሲነገር ብዙዎችም ታርጋቸውን ቀድመው በመፍታት አድማውን ተቀላቅለዋል።
የአገዛዙ ካድሬዎችም ታርጋ እየፈቱ መሆናቸውን ነው የተነገረው።
ታርጋ የተፈታባቸው ባለባጃጆች በአቋማቸው በመጽናት ስራ አለመጀመራቸውም ታውቋል።
በደብረታቦር አድማው መቀጠሉ ያስደነገጣቸው የአካባቢው ካድሬዎች ከፍተኛ ወታደር በከተማው እንዲሰማሩ ቢያደርግም ሕዝቡ በምንም ማስፈራሪያ አንበገርም ብለዋል ሲሉ ለኢሳት መረጃውን ያደረሱ ምንጮች ይገልጻሉ።
በዛቻውና ማስፈራሪያው የተደናገጡ ባይኖሩም የስርአቱ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ 3 ባጃጆች በከተማው ብቻቸውን ውርውር እያሉ መሆናቸው ተነግሯል።
የተወሰኑ የጤፍና የበቆሎ መጋዘን ቤቶች ዛቻውን በመፍራት ቢከፍቱም ሕዝቡ በአድማው አንሳተፍም የሚሉ የአገዛዙ ካድሬዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ እየገለጸ ይገኛል ተብሏል።
በደብረታቦር ውጥረቱ እያየለ ከመሄዱ ሌላ ወደ አድማው የገቡት የከተሞች ቁጥርም እየጨመር መጥቷል።
በወልዲያና በወረታም ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ነው የተገለጸው።
በምስራቅ ጎጃም ደምበጫም አድማው መጀመሩ ተነግሯል።
በባህርዳርም ውጥረቱ ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል።በከተማዋ መውጫ መግቢያ ጠንከር ያለ ፍተሻ እየተደረገ ይገኛል።
በድባንቄ፣ በኦዴት መውጪያ እንዲሁም በአባይ ማዶ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።