በደቡብ ሱዳን ለተቀናቃኞች ምህረት የሚያስገኝ አዋጅ ይፋ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 3/2010) የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ለተቀናቃኞቻቸው ምህረት የሚያስገኝ አዋጅ ይፋ  አደረጉ።

ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ሙሉ የምህረት አዋጁን ይፋ ያደረጉት ከካርቱሙ የሰላም ስምምነት በኋላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የምህረት አዋጁ በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ይፋ ተደርጓል።

ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የሰጡት ምህረት የቀድሞው የደቡብ ሱዳንን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን ጨምሮ የትጥቅ ትግል ይሚያደርጉ አማፅያን ጭምር የሚያካትት ነው።

የምህረት አዋጁ ይፋ የተደረገው በደቡብ ሱዳን መንግስታዊ መዋቅር የስልጣን ክፍፍል ለማድረግ በሱዳን ካርቱም የተደረሰውን የማጠቃለያ ስምምነትን ተከትሎ ነው፡፡

ሬክ ማቻር ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ከተጋጩ በኋላ የምክትል ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን ትተው ጫካ መግባታቸው ይታወሳል።

በኋላ ላይም ወደ ደቡብ አፍሪካ ሂደው በስደት መኖር ጀምረው ነበር።

ሁለቱን ተቀናቃኞች ለማስታረቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጎሬቤት ሀገራት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቢቆዩም ሳይሳካ ቆይቷል።

አሁን ግን በካርቱም አደራዳሪነት የተካሄደው ስምምነት መስመሩ ተነግሯል። እናም ይሕንን ተከትሎም የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ለተቀናቃኞቻቸው ምህረት የሚያስገኝ አዋጅ ይፋ  አድርገዋል ።

የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ግን ፕሬዝዳንቱ አስረዋቸው ለሚገኙ የፖለቲካ እስረኞችም ጭምር ምህረት ተደርጎላቸው ሊለቀቁ ይገባል ብለዋል፡፡