በዘጠኙ የዓየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።

በዘጠኙ የዓየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 02 ቀን 2011 ዓ/ም ) የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ነሃሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ያቀረቡት ጥያቄን ተከትሎ የሥራ ማቆም አድማ ባደረጉት በዘጠኙ የዓየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የ14 ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ በማድረግ ፍርድ ቤቱ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።
መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ቃል መቀበል፣ አሻራ እና ፎቶ ማንሳት ጨምሮ የሦስት ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ለችሎቱ አስረድቷል። የስልክ ልውውጥ ማስረጃ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ቢሮ ለማቅረብ፤ በአየር መንገዱ ላይ በተጠርጣሪዎቹ ምክንያት የደረሰውን የገንዘብ ኪሳራ ማስረጃ ለመሰብሰብ፤ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ያልተያዙ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ለመያዝ፣ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ማስረጃዎች ለማምጣት እና ተጨማሪ የምስክር ቃል ለመቀበል እንዲያስችለው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ተከሳሾቹ በበኩላቸው ”የጠየቅነው የመብት ጥያቄም ሆነ የስራ ማቆም አድማ ህገመንግስታዊ መብታችን ነው። ፖሊስ ያቀረባቸው ክሶች ተገቢነት የላቸውም። ከሌሎች ክልል ሰራተኞች ጋርም የሚያገናኘን ነገር የለም። ስራ ማቆም አድማ ከማድረጋችን አስቀድሞ ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ አሳውቀናል። የአቬሽኑን ሰራተኞች ስለሆንን የአየር መንገዱ ኪሳራ እኛን አይመለከተንም። ስለዚህም ለስራው አስፈላጊ በመሆናችን በስራ ገበታችን እያለን ፖሊስ ምርምመራውን መቀጠል ይችላል። ችሎቱ ይህን አይቶ የዋስትና መብታችንን ሊፈቀድልን ይገባል።” ሲሉ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት ለችሎቱ አስታውቀዋል።
ተጠርጣሪዎች ከሌሎች አባሪ አካላት ጋር በመሆን ሴራ የታከለበት እንቅስቃሴ አድርገዋል። ዲያስፖራው መግቢያ ሰዓት ላይ ዲያስፖራውን በማወክ የአየር መንገዱን በማስተጓጎል ሆነ ብለው ሌሎችንም ለአድማ አነሳስተዋል። ሰራተኞችን መደበኛ ስራቸውን እንዳይሰሩ ሲከለክሉ ነበር። በተጨማሪም ገቢና ወጪ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ እንዳይወጡ ‘ቆዩ’ ‘ዘግየት በሉ’ በማለት አየር መንገዱ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት ስለማድረጋቸው የምስክር ቃል መቀበሉን በመግለጽ መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን የክስ መቃወሚያ ተቃውሟል።
ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ፖሊስ እና የተተርጣሪዎቹ ጠበቆች ያቀረቡትን አቤቱታ ከሰማ በኋላ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፤ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለመስከረም 8 ቀ 2011 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።