በዓለም ላይ ለ128ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ42ኛ ጊዜ የሚዘከረውን የላባደሮች ቀን -ሜይ ዴይን ምክንያት በማድረግ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ።

ሚያዝያ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ በሊባኖስ፣ እንዲሁም በስዊድንና በኖርዌይ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባደረጓቸው የተቃውሞ ሰልፎች በአኢትዮጵያ ውስጥ በነገሠው አምባገነን አገዛዝ የሠራተኛውም ሆነ የሁሉም ዜጋ መብት መረገጡን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።
ሰላማዊ ዜጎችና ንጹሀን ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ሳቢያ በእስር እየማቀቁ በሚገኙባት ኢትዮጵያ የዓለም ላባደሮች ከመቶ ዓመት በፊት የተቀዳጇቸው መብቶች ሊከበሩ እንዳልቻሉ የጠቀሱት ሰልፈኞቹ፤ “እኛ ሶሻል ዲሞክራቶች ነን! አቋምና አሰላለፋችን ከተበደለው ሕዝባችን ጎን ነው!!” ብለዋል።
በሊባኖስ፣ ኦስሎና በስቶኮሆል በተካሄዱት በነኚህ ሰልፎች ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በመገኘት ለወገኖቻቸው ድምጻቸውን ሢያሰሙ ውለዋል። የአኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡና የተለያዩ መፈክሮችን እያሰሙ ወደ ኖራ ባንቶርጌት የተጓዙት የስዊድን ሰልፈኞች ፣ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች አስመልክቶ ከስቶኮሆልም ከንቲባ የተላለፈላቸውን መልዕክት ሰምተዋል።
“መስዋዕት” በተሰኘ አስተባባሪ ግብረ ኃይል የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉት በሊባኖስ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስፍራው የሚገኘው የቆንጽላ ስህፈት ቤት አድሎ አሰራር እንዲቆም፣ የዜግነት መብታቸው እኩል እንዲከበርና የቆንጽላ ጽህፈት ቤቱ ቅጥር በፖለቲካዊ ወገንተኝነት ሳይሆን በችሎታ እንዲሆን ጠይቀዋል።
በዜጎች መካከል አድሎ ይፈጽማል ያሉትን የቆንጽላ ጽህፈት ቤት ሰልፈኞቹ አጥብቀው አውግዘዋል።