በኬንያ የተሰማሩ የኢትዮጵያና ኬንያ ወታደሮች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃ ይወስዳሉ ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2009)

በሶማሊያ ተሰማርተው የሚገኙ የኢትዮጵያና የኬንያ ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃን ይወስዳሉ ሲል በእርዳታ ድርጅቶች የወጣ አለም አቀፍ ሪፖርት ገለጸ።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ ልዩ ፖሊስ በመባል የሚታወቁ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት በሶማሌ አርብቶ አደሮች ላይ የጾታ ጥቃትን ያካተተ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸማቸውን ቪኦኤ የሶማሌኛው ክፍል ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ይኸው በዜና ተቋሙ የእንግሊዝኛ ክፍል የቀረበው ዘገባ የኢትዮጵያ ወታደሮች ፈጽመውታል ከተባለው የአስገድዶ መድፈር ድርጊት በተጨማሪ የአካል ጉዳትን እንደሚፈጽሙ አስነብቧል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ከምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ የተፈናቀለ ሃሰን ሞሃመድ ሙክታር የተባለ ሶማሊያዊ ሩቂያ የተባለች ታላቅ እህቱ ከ15 ወር በፊት በልዩ ፖሊስ ባሪ ወደ ተባለ የኢትዮጵያ ከተማ መወሰዷን ለቪኦኤ ገልጿል።

የእህቱ ባል በአንድ ወቅት ከአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ጋር በመተባበሩና 100 የአሜሪካ ዶላር በመቀበሉ ምክንያት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድርጊቱን ሊፈጽሙ እንደቻሉ ሃሰን አስረድቷል።

አለም አቀፍ ሪፖርቱ በሶስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና አብረዋቸው የሚሰሩ የእርዳታ ተቋማት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ኬንያ በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ካሰማሩት ወታደር በተጨማሪ ድንበሮቻቸውን የሚጠብቅ ሃይል አስርገው እንዲሚገኙ ታውቋል።

ከሰላም አስከባሪ ልዑካን ቡድኑ ውጭ ያሉት እነዚሁ ሁለት ሃገራት ወታደሮች እየፈጸሙ ያለው ህገወጥ ድርጊት በተጠያቂነት ላይ ግራ መጋባትን ፈጥሮ እንደሚገኝም ሪፖርቱ የተለያዩ ክስተቶችን ዋቢ በማድረግ አብራርቷል።

ልዩ ፖሊስ በመባል የሚታወቁት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2007 አም መቋቋማቸውን ያወሳው ሪፖርቱ በሶማሌ ክልል በኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ላይ ወታደራዊ ዕርምጃን የመውሰድ ተልዕኮ እንደነበራቸው አመልክቷል።

ይሁንና የክልሉ ፖሊስ አባላቱ በሶማሌ ክልል ጭምር የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልፁ ቆይተዋል። ከወራት በፊት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል በኢትዮጵያ ወታደሮች ተፈጽሟል የተባለን የሰላማዊ ሰዎች ግድያን ምርመራ እንዲያካሄድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጥያቄ ማቅረባቸውም ይታወሳል።

አለም አቀፍ ሪፖርቱ በኬንያ ወታደሮችም የጅምላ እስራትን ያካተተ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም እንደነበር የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አቅርቧል።

ይሁንና የኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጆሴፍ አ’ውቶ የሃገራቸው ወታደሮች ፈጽመውታል የተባለውን ድርጊት አስተባብለዋል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁንድ ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።