በኦሮሚያ 955 ትምህርት ቤቶች ስራ ጀመሩ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2011)በኦሮሚያ ክልል ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ተዘግተው ከነበሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 955ቱ ስራ መጀመራቸው ተገለጸ።

የሃገር ሽማግሌዎችና የሚመለከታቸው ወገኖች ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት ትምህርት ቤቶቹ መከፈት መቻላቸውን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ በ6 ዞኖች ማለትም በምዕራብ ጉጂ፣በምስራቅ ወለጋ፣ምዕራብ ወለጋ፣በቄለም ወለጋ፣በሆሮጉድሩ ወለጋና በቦረና ዞኖች በአጠቃላይ በጸጥታ ችግር 1ሺ 765 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውም ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ከሃገር ሽማግሌዎችና ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በተደረገ ጥረት ከተዘጉት ትምህርት ቤቶች 955ቱ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ተከፍተው ስራቸውን መጀመራቸውን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።