በኤሌክትሪክ መቆራረጥ የተነሳ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2011)በኤሌክትሪክ መቆራረጥ የተነሳ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታችውን በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ።

መንግስት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በፈረቃ ሊያደርገው መሆኑን ዛሬ አስታውቋል።

ኢሳት ያነጋገራቸው በሀዋሳ፣ በአዲስ አበባ፣ በባህርዳርና አዳማ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ሰሞኑን የተከሰተው የሃይል መቆራረጥ ያልተለመደ በመሆኑ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሃይል መቆራረጡ የተከሰተው በግድቦች በቂ ውሀ ባለመኖሩ ምክንያት የተፈጠረ ነው ብሏል።

ችግሩ ለሱዳንና ለጅቡቲ የሚቀረበውን የኤሌክትሪክ ሽያጭም እንደሚቋረጥ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሃይል መቆራረጡ በበርካታ ከተሞች መከሰት ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።

ከዚህ በፊት ከሚከሰተው በተለየ ሁኔታ ከአንድ ሳምንት ወዲህ የሚታየው መቆራረጥ ያልተለመደና በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ነው ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የሚገልጹት።

በሀዋሳ በጸጉር ቤት ስራና ማተሚያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ነዋሪዎች እስከሁለት ቀናት መብራት ተቋርጦ የሚቀርበት ጊዜ በመኖሩ በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል።

መስራት ከማንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት። በአዲስ አበባም ባለፉት አምስት ቀናት ባልተመለደ ሁኔታ የሚታየው የሃይል መቆራረጥ የመኖር ህልውናን በሚፈታተን መልኩ ለአደጋ እንዳጋለጣቸው ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት።

በመብራት ላይ የተመሰረተ የንግድ ስራ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ችግሩ እያስከተለ ያለው ጉዳት በልቶ ማደርን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እስከመሆን ደርሷል ነው የሚሉት።

በባህርዳርና አዳማም ተመሳሳይ የህዝብ እሮሮዎች በርክተው ይሰማሉ።

ባህርዳር የመብራት መቆራረጡ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ነዋሪዎች በምሬት ይገልጻሉ።

ለቀናት የዘለቀውን የህብረተሰቡን ጥያቄ መንግስት ዛሬ ምክንያቱን በመግለጽ መግለጫ ሰጥቷል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሰጠው በዚሁ መግለጫ የሃይል መቆራረጡ የተከሰተው በግድቦች ውስጥ የውሃ ክምችት በመቀነሱ ነው ብሏል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ እንዳሉት የሃይል ማመንጫ ግድቦች በዝናብ እጥረት ምክንያት በቂ ውሃ ባለመያዛቸው የተፈለገውን ሃይል ማመንጨት አልቻሉም።

ግልገል ጊቤ ቁጥር ሶስት ማመንጨት ካለበት በአንድ ሺህ ሜጋ ዋት ያነሰ ሃይል ብቻ እየሰጠ በመሆኑ የሃይል መቆራረጥ ሊከሰት ችሏል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ይህንን ችግር በጊዜያዊነት የሚቀርፍ የፈረቃ ፕሮግራም መዘጋጀቱን የገለጹት ዶክተር ስለሺ እስከ ሰኔ 30 የሚዘልቅ የፈረቃ ፕሮግራም ተዘርግቷል ብለዋል።

ከግንቦት አንድ ቀን የጀመረው የፈረቃ ፕሮግራም በቀን ለአምስት ሰዓት መብራት የሚቋረጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የምግብ ማቀነባበሪያዎች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት 24 ሰዓት ኃይል ማግኘታቸውን የሚቀጥሉና ፈረቃ ውስጥ የማይገቡ መሆኑም በመግለጫው ተነግሯል፡፡

በሃይል መቆራረጥ ምክንያት ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለጅቡቲ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ሃይል እንደምታቋርጥም ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል።