በኢንጅነር ታከለ ኡማና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መካከል ውይይት ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 30/2011)በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መካከል ውይይት መደረጉ ተገለጸ።

ራሱን የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት በሚል የሚጠራው አካል ባወጣው መግለጫ  እንዳስታወቀው በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው ውይይት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በመስማማት ተጠናቋል።

በከተማዋ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ ለጠየቀው የባልደራስ አመራር የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጥያቄውን በመቀበል አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል።

ስምምነቱን ተከትሎም ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚያደርግ ባላደራ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ በሚል የሚታወቀው ስብስብ ከምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር ያደረገውን ውይይት በተመለከተ እንደገለጸው በቀጣይ ሰላማዊ የሆነ ትግል ለማካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ለኢሳት እንደገለጸው የዛሬው ውይይት ለቀጣይ እንቅስቃሴያቸው መልካም ውጤት የተገኘበት ነው።

በጋዜጠኛ እስከንድር ነጋ ሰብሳቢነት የሚንቀሳቀሰው የባላደራ ምክር ቤቱ በተደጋጋሚ ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ያቀዳቸው መድረኮች መደናቀፋቸው በውይይቱ መነሳቱን የገለጸው ጋዜጠኛ ኤልያስ በቀጣይ ስብሰባዎች መካሄድ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይም ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ንግግር እንዲደረግ የሚፈልጉ ወገኖች በዛሬው ዕለት በኢንጅነር ታከለ ኡማና በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መካከል የተደረገውን ውይይት ጥሩ ጅምር ሲሉ አወድሰውታል።

የባላደራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እንደሚለውም የሰለጠነ ውይይት ለችግሮች መፍትሄ አመንጪ ብቸኛ መንገድ እንደሆነ ይገልጻል።

ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጋር የተጀመረው ውይይትም ለሰለጠነ የመፍትሄ አቅጣጫ ጥሩ ጅምር ነው ይላል።

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት በሚል የሚንቀሳቀሱት የመብት ተሟጋቾች ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ህዝቡን ሊያወያዩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በምርጫ ህዝቡ የአዲስ አበባን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጪያ መድረኮች በሁሉም የአዲስ አበባ አካባቢዎች እንደሚደረግ ነው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ለኢሳት የገለጸው።