በኢትዮ-ሶማሌ ክልል አሁንም ዜጎች ወደ ሃረር ከተማ እየተሰደዱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 4/2010)በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ተከስቶ ከነበረው ቀውስ ጋር ተያይዞ አሁንም ዜጎች ወደ ሃረር ከተማ እየተሰደዱ ነው ተባለ።

ሐረር ከገቡት ስደተኞች መካከልም ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ መኖራቸው ታውቋል።

በጅጅጋ በአብያተክርስቲያናት ተጠልለው የሚገኙት ዜጎች አሁንም ምንም አይነት እርዳታ እንዳልተሰጣቸውና ሕይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑ ተሰምቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የፌደራሉ መንግስት በጅጅጋ ከተማ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ80 ሚሊየን ብር የሚበልጥ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ኣያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ከጅጅጋ ተነስተው በሀረር ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ በልዩ ስሙ በሸንኮር ሞዴል ትምህርት ቤት ውስጥ ደረሱ የተባለው 300 ያህል ስደተኞች ናቸው።

በመጠለያው የደረሱት ስደተኞች ሌሎች ስደተኞችም እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ስደተኞችም ወደ ሃረር ለመምጣት መንገድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለስደተኞቹ የሃረር ከተማ ነዋሪዎችና የከተማዋ አስተዳደር ሰራተኞች ምግብ ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ኣያደረጉላቸው መሆኑን ተናገረዋል።

ሰሞኑን ጨምሮ ወደ ሃረር ከተሰደዱት መካከልም ቁጥራቸው ሁለት መቶ የሚጠጋ ስደተኞች ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸውን ኢሳት ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በየአብያተክርስቲያናትም ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞችም ምንም አይነት እርዳታ ባለማግኘታቸው የከፋ ችግር መግባታቸውን መረጃው ጨምሮ ገልጿል።

በአካባቢው ያለው የኢንተርኔት ችግርም ከጅጅጋ ውጪ ባሉ ከተሞች እየደረሰ ያለውን ጉዳት በትክክል ማወቅ አለመቻሉን የኢሳት ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን  የአቅርቦትና ሎጅስቲክ ዳይሬክተር አቶ አይድሩስ ሀሰን በጅጅጋና አካባቢው ያለው ችግር ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ ድጋፉ በአፋጣኝ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉም 7ሺህ 5 መቶ ኩንታል ሩዝ ፣ 5ሺህ ኩንታል አልሚ ምግብ፣ 8ሺህ ሊትር ዘይት ፣ 5 ሺህ ኩንታል ብስኩትና 3 ሺህ ኩንታል ዱቄት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታው በፍጥነት ለማድረስ ከተሽከርካሪ በተጨማሪ ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአውሮፕላን ለማድረስም እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

እርዳታውን ከድሬዳዋና ከአዳማ የእህል መጋዘን ለማድረስ ስራው ተጀምሯልም ነው ያሉት።

ከድሬዳዋ መጋዘን የተጫነው የእርዳታ እህል በአፋጣኝ እንደሚደርስና ለተረጂዎች እንደሚከፋፈል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮ-ሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ባሉ አብያተ-ክርስቲያናት ተጠልለው የሚገኙ ከ10ሺህ የሚበልጡ አባወራዎች እንዳሉም ክልሉ አስታውቋል፡፡