በኢትዮጵያ 36 ሚሊየን ህጻናት በከፋ ድህነት እየተሰቃዩ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 9/2011)በኢትዮጵያ እድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 36 ሚሊየን ህጻናት በከፋ ድህነት እንደሚሰቃዩ ተገለጸ።

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣንና በዩኒሴፍ ትብብር በተዘጋጀ አንድ ጥናት ላይ እንደተመለከተው ከ41ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ህጻናት 88በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ የድህነት መለኪያዎች አደጋ ውስጥ ናቸው።

ፋይል

ጥናቱ በዘጠኝ የድህነት ማሳያ መስፈርቶች ውስጥ ቢያንስ በሶስቱ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንዳሉ የሚጠቁም እንደሆነ አመላክቷል።

በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ የወደፊት የኢኮኖሚ ብልጽግናና የማህበራዊ ልማት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መውደቁ እንደማይቀር በጥናቱ ተገልጿል።

በጥናቱ የተመለከቱት ዘጠኙ መለኪያዎች ልማት፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ጤና፣ ውሃ፣ ንጽህና፣ መኖሪያ ቤት፣ ትምህርት፡ መረጃና ተሳትፎ ናቸው።

አንድ ህጻን ከእነዚህ መለኪያዎች ከ3 እስከ ስድስት ያሉትን ካላሟላ በፍጹም ድህነት የሚሰቃይ በሚል እንደሚፈረጅ በ32 የአፍሪካ ሃገራት ላይ ተግባራዊ በሆነ ዓለምዓቀፍ የመለኪያ ዘዴ ላይ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያውያን ህጻናት ላይ የተደረገው ጥናት ከእነዚህ መለኪያዎች በሶስቱ ላይ ያተኮረ መሆኑን ነው በማዕከላዊ ስታስቲክስና በዩኒሴፍ ትብብር ይፋ የተደረገው ሪፖርት ላይ የተመለከተው።

በዚህም መሰረት 41 ሚሊዮን ከሚሆኑት እድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ህጻናት መካከል 88 በመቶዎቹ በከፋ ድህነት የሚሰቃዩ ናቸው።

ይህም 36ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ህጻናት መሰረታዊ የሆኑትን ነገሮች ባላማግኘታቸው በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀዋል ይላል ጥናቱ።

መኖሪያ ቤትና መሰረታዊ ንጽህና አለማግኘት የኢትዮጵዮጵያውያን ህጻናትን ሰቅዘው የያዙ ችግሮች በሚል ከተዘረዘሩት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የትምህርት እጦትና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘትም ብርቱ ፈተናዎች ተብለው ተቀምጠዋል።

እነዚህ ችግሮች ህጻናቱ በአካል ቀንጭረው በአእምሮና ማህበራዊ እድገቱ ጫጭተው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል ተብሏል።

ጥናቱ እንዳመለከተው የህጻናት ስቃይ በከፍተኛ ደረጃ ከሚታይባቸው አካባቢዎች የገጠሩ ክፍል በዋናነት ተጠቅሷል።

በገጠር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህጻናት መካከል 94 በመቶ የሚሆኑት በከፋ ድህነት የሚሰቃዩ ሲሆኑ በከተማ ደግሞ 42 በመቶ የዚሁ ችግር ተጠቂ እንደሆኑ ተገልጿል።

አዲስ አበባ 18በመቶ ህጻናት በድህነት የሚሰቃዩባት በሚል አነስተኛ ቁጥር ስታስመዘግብ፣አፋር፣አማራና ደቡብ ክልሎች 91 በመቶ የችግሩ ተጠቂ ህጻናት የሚኖሩባቸው ተብለው ተጠቅሰዋል።

ከቆዳ ስፋትና ከህዝብ ቁጥር አንጻር ደግሞ የኦሮሚያ፣የአማራና የደቡብ ክልሎች በከፋ ድህነት የሚሰቃዩ ሕጻናት የተመዘገቡባቸው አካባቢዎች ተብለዋል።

በእነዚህ ክልሎች ብቻ 34 ሚሊየን ሕጻናት ሲመዘገቡ በተቀሩት አካባቢዎች 2 ሚሊየን ሕጻናት በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።

በአጠቃላይ መለኪያ ዘጠኙን መስፈርቶች በማሟላት በቂ አገልግሎት የሚያገኙ የኢትዮጵያ ሕጻናት ቁጥር 1 በመቶ ብቻ እንደሆነ በጥናቱ ላይ ሰፍሯል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ የኢትዮጵያን መጪ ጊዜ ስጋት ውስጥ እንደከተተው ነው ጥናቱ ያመለከተው።

የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚረከቡት የዛሬዎቹ ሕጻናት በዚህ ስቃይ ውስጥ የሚቀጥሉ ከሆነ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብልጽግናም ሆነ ህልውና እንዲሁም ለማህበራዊ እድገቱ አሳሳቢ አደጋን ከወዲሁ ደቅኗል ብሏል ጥናቱ።