በኢትዮጵያ የተከሰተው የሰብል ተምች በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የተከሰተው የሰብል ተምች በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑ ተገለጸ። የሰብል ተምቹ እስካሁን ባለው ሁኔታ በደቡብ ክልል ያሉትን ሁሉንም ዞኖች ያጠቃ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በኦሮሚያ ደግሞ ሰባት የሚሆኑ ዞኖች እየተስፋፋ ባለው የሰብል ተምች መጎዳታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል። 

ተምቹ የምስራቅና የምዕራብ አማራ ክልል አካባቢዎችን እንዲሁም በጋምቤላ እኛ ቤኒሻንጉል ጉምዝም ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው “አርሚ ወርም” የተሸኘው የሰብል ተምች በሃገሪቱ 35 ወረዳዎች 146ሺ 320 ሄክታር ላይ ተሰራጭቷል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው አርሚ ወርም የተሰኘው ትል የደረሱ ሰብሎችን በመመገብ ከፍተኛ ጥፋት የሚያደርስ ተምች ነው።

የሰብል ተምቹን ለመከላከል የግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር 35ሺ ሊተር ኬሚካሎች ገዝተው ቢያሰራጩም ችግሩ አሁንም ድረስ እየተስፋፋ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ 7.7 ሚሊዮን ህዝብ በድርቅ ሳቢያ ለምግብ እጥረት በተዳረገበት ሁኔታ የሰብል ተምቹ በመላ ሃገሪቱ በምርት ላይ ጥቃት ማድረሱ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያሉትን ብሄል ማስከተሉን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የሰብል ተምቹ መነሻው ደቡብና ሰሜን አሜሪካ ቢሆንም በአሁን ጊዜ በአፍሪካ በዛምቢያ፣ ማላዊ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ እና ሌሎችም የአፍሪካ ሃገራት ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ታውቋል።

ይህ “አርሚ ዎርም” የተሰኘው የሰብል ተምች በእሲያና በሜዲትራኒያን ሃገሮች ሊስፋፋ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ስጋቱን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የተከሰተው የሰብል ተምች ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም፣ በሃገሪቱ ባለው አገዛዝ ዘንድ ብዙ ትኩረት አለማማግኘቱን ታዛቢዎች ይነገራሉ።