በኢትዮጵያ የሚከሰቱት ግጭቶች በአንድ ማዕከል እንደሚቀነባበሩ የድህንነት መስሪያ ቤት አስታወቀ

በኢትዮጵያ የሚከሰቱት ግጭቶች በአንድ ማዕከል እንደሚቀነባበሩ የድህንነት መስሪያ ቤት አስታወቀ
( ኢሳት ዜና መስከረም 08 ቀን 2011 ዓ/ም ) የብሄራዊ ድህንነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያም ሆነ በሶማሊ ክልል የተፈጠሩት ግጭቶች አላማቸው አንድ ነው ብሎአል። በአዲስ አበባ ዙሪያ የተከሰተው ግጭት በሶማሊ ክልልና በሌሎችም አካባቢዎች የተፈጠሩት ግጭቶች ተቀጽላ ነው። የግጭቶች ዋና አላማ የለውጡን እንቅስቃሴ መግታትና በመስከረም ወር የሚካሄደውን የኢህአዴግ ጉባኤ ማደናቀፍ ነው ያለው የደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ሁከቱ በትናንሽ ችግሮችና ልዩነቶች የሚነሳ ሳይሆን በታቀደ መልኩ የሚከናወን፣ ድብቅ ፖለቲካዊ አላማ ያለው እና አገሪቱን በማያባራ ግጭት ውስጥ በመክተት ለውጡን ለማሽመድመድና ለመቀልበስ የሚደረግ ሴራ ነው ብሎአል።
የደህንነት ምክር ቤቱ ለዜጎች ህይወት ዋስትና ለመስጠት መንግስት ማንኛውንም ህጋዊና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩንና ድርጊቱም እንደሚቀጥል ገልጿል።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ልዩነትን በሚያሰፉና ብጥብጥን በሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃሁን መሰብሰብ ይኖርባችኋል ሲል የደህንነት መስሪያ ቤቱ ጠንካራ መግለጫ አውጥቷል።
የደህንነት ምክር ቤቱ ግጭት ያቀናብራሉ ያላቸውን ሃይሎች በስም አልጠቀሰም። ላለፉት 6 ወራት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ሲከሰቱና ግጭቶቹ አንድ አላማ ለማስፈጸም በሚል በተወሰነ ሃይል ከተቋቋም፣ የደህንነት ምክር ቤቱ ግጭቶችን የሚያስቆም ጠንካራ እርምጃ ለምን አልወሰደም፣ አሁንስ ቢሆን የግጭት መፈልፈያ ምክንያቶችን ለይቶ አውቋል ወይ የሚል ጥያቄ እየቀረበበት ነው።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ በተለይ በቡራዩ በህዝብ ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ብዙዎች በመንግስት ላይ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። መንግስት ለምን ችግር ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ የጥንቃቄ እርምጃ አልወሰደም፣ ችግሩ እንደተከሰተስ ለምን ለማስቆም አልቻለም የሚሉ ጥያቄዎች በብዛት የቀረቡ ሲሆን፣ የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ፣ በቡራዩ አካባቢ ግጭት የሚያስነሳ ምክንያት እንዳልነበረ በመናገር ለጥያቄው መልስ ሰጥተዋል።