በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻል እንደነበር ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 15/2011)በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻል ነበር ሲል የአሜሪካን አውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ ቃል አቀባይን ጠቅሶ ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው ባለፈው ህዳር ወር የአሜሪካን አውሮፕላን አብራሪዎች አባላት ለቦይንግ ኩባንያ ችግሩን አስረድተው ጥንቃቄ እንዲደረግ ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ አደጋ ሊከሰት አይችልም ነበር ብለዋል።

የቦይንግ ኩባንያ የአደጋውን መንስዔ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርባቸውን ምክንያቶች የአብራሪዎቹ ማህበር ቃል አቀባይ ይቅርታ የሌለው ጥፋት ሲሉ አውግዘውታል።

በአሜሪካን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያው አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ መንስዔው ላይ ክርክሩ በተጋጋለበት በዚህን ወቅት የአሜሪካን አብራሪዎች ማህበር መግለጫ ለቦይንግ ኩባንያ ትልቅ ኪሳራ ሊያመጣ ይችላል እየተባለ ነው።

በአሜሪካን ቴክሳስ ግዛት የዓለም የአቬዬሽን ተቆጣጣሪዎች ጉባዔ ዛሬ ተጀምሯል። 33 ሀገራት በጉባዔ በመካፈል ላይ ናቸው።

57 ድርጅቶችን የወከሉ የዘርፉ ባለሙያዎችም ቴክሳስ ገብተዋል።

በጉባዔው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ የተመለከተው ጉዳይ የቦይንግ ኩባንያንና የአሜሪካን አውሮፕላን አብራሪዎችን ፍጥጫ ውስጥ መክተቱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ቦይንግ ኩባንያ ማክስ 737 በተሰኘው አውሮፕላን ምርቱ ላይ የተነሳበት ጥያቄ የኩባንያውን ስምና ክብር ከማጉደፉም በላይ ለኪሳራ እየዳረገው እንደሆነ ይነገራል።

ይህንን ኪሳራ ለመቀልበስና ስሙን ለመመለስ ቦይንግ ኩባንያና የአሜሪካን ሪፐብሊካን ፓርቲ መሪዎች የአደጋውን መንስዔ በወፎችና በአብራሪዎቹ ላይ በማላከክ ዘመቻ መጀመራቸው ውዝግብን ፈጥሯል።

ዛሬ በቴክሳስ በተጀመረው ጉባዔ ላይ የአሜሪካን አብራሪዎች ማህበር ቃል አቀባይ በቦይንግ ኩባንያ እየቀረቡ ያሉ ሰበቦችን አሳፋሪ ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ባለፈው ህዳር ወር ላይ የቦይንግ ኩባንያ አመራሮች ከአሜሪካን አውሮፕላን አብራሪዎች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ዴኒስ ታጀር በአብራሪዎቹ የተጠቆሙትን ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች የቦይንግ ኩባንያ ጆሮ ዳባ ልብስ ብለዋል ሲሉ ጣታቸውን ቦይንግ ላይ ቀስረዋል።

ያን ጊዜ በአብራሪዎቹ የተሰጡትን ሀሳቦች ቦይንግ ቢቀበላቸው ኖሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰን አደጋ ማስቀረት ይቻል ነበር ብለዋል ቃል አቀባዩ።