በኢትዮጵያ ምድር ተሳዳጅም አሳዳጅም ሊኖር አይገባም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 3/2011) በኢትዮጵያ ምድር ተሳዳጅም አሳዳጅም ሊኖር አይገባም ሁላችንም ተከባብረን መኖር ይገባናል ሲሉ ብጹእ አቡነ አብርሃም ጥሪ አቀረቡ።

          ቋንቋ ለመግባቢያ እንጂ ለመለያያ መሆንየለበትም ያሉት ብጹእ አቡነ አብርሃም ሰዎች በአደባባይ ተቀጥቅጠው የሚገደሉበትና በአደባባይ በሚሰቀሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የሃይማኖትሃገር ነች ብሎ መናገሩም የሚያሸማቅቅ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

 ዜጎች ከግብረገብ ድርጊቶች እንዳያፈነግጡም መክረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የናህርዳር ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብጹእ አቡነ አብርሃም ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አባቶች መካከል ስለተካሄደው እርቅና ስለቤተክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ሁኔታም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህርዳር ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብጹእ አቡነ አብርሃም ከኢሳት ጋር ባደረጉት በዚህ ቃለ ምልልስ የሃይማኖት አባቶች በሕዝብና በሃገር ላይ የሚደርሰውን በደል በዝምታ እንዳልተመለከቱትና በሚችሉት አጋጣሚ ሁሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ተቃውሞና ውግዘታቸው ሌላ የከፋ ሁኔታ እንዳያስከትል በጥንቃቄ ሲጓዙ መቆየታቸውንም አመልክተዋል።

በመስከረም 2009 በደመራ እለት በባህር ዳር ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘው ያሰሙት ንግግር የዚሁ ሒደት አካል ነው ብለው በዚያ ንግግራቸው ከመንግስት የገርጠማቸው ችግር እንዳልነበረም አስታውሰዋል።

ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ለ4ኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስና ለሌሎች አባቶች መሰደድ ምክንያት የሆነውና በአባቶች መካከል ልዩነት የፈጠረው ችግር እንዲፈታ ከሃገር ቤት ለዕርቅ ከተላኩት ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ የነበሩት አቡነ አብርሃም ስለ ዕርቁ ሂደትና ወጤት ለኢሳት ገልጸዋል።

ለዕርቅ ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በቤተመንግስት ስለነበራቸው ቆይታ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ አብርሃም የዕርቅ ሂደቱ እንዲሳካ በሃገር ቤትም ፓትርያርኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የራሳቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም አስተያየታቸውን የሰጡት ብጹዕ አቡነ አብርሃም በኢትዮጵያ ምድር አሳዳጅና ተሳዳጅ ሊኖር አይገባም፣ ቋንቋም መግባቢያ እንጂ መለያያ አይደለም ሲሉም አሳስበዋል። በባዕድ ሃገር በስደተኝነት እያኖርን የገዛ ወገናችንን ዕትብቱ ከተቀበረበት ከኢትዮጵያ ምድር ክልልህ አይደለም እያለ ማሳደድ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ተከባብረውና ተግባብተው እንዲኖሩና ከነውር ድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጥሪ አቅርበዋል። ለጥፋትና ለጉዳት መራቀቅ አያስፈልገንም፣ ከግዜያዊ ስሜትና ዕብሪትም መታቀብ ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ አቡነ አብርሃም ዜጎች በአደባባይ በድንጋይ ተቀጥቅጠው የሚገደሉበትና በአደባባይ የሚሰቀሉበትን የነውር ድርጊት ኮንነዋል።