በኢትዮጵያ ሕገ መንግስቱና የፌደራል ስርአቱ እየተጣሰ ነው

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) በኢትዮጵያ ሕገ መንግስቱና ፌደራል ስርአቱ እየተጣሰ መሆኑን ሕዝቡ ተገንዝቧል ሲሉ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

የሕወሃት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ዛሬ የተጀመረውን የሕወሃት ጉባኤ በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ትምክህተኛው ሃይል ስርአቱን ለማፍረስና ወደ ኋላ ለመመለስ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉም ከሰዋል።

27 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሁሉ ጨለማ ነው ብሎ መናገሩም ሆነ ሁሉንም ነገር ከሕወሃት ጋር ማያያዙም ተገቢ እንዳልሆነ አሳስበዋል።

ዛሬ በመቀሌ የተጀመረው የሕወሃት ጉባኤ ታሪካዊና ልዩ ወሳኔዎች የሚጠበቁበት እንደሆነ የገለጹት የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በቀጣይ በሚካሄደው የኢሕአዴግ ጉባኤም የስራ አስፈጻሚና የምክር ቤት አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ እንደሚኖርም አመልክተዋል።

በዚህ የኢሕአዴግ ጉባኤ ፕሮግራማችንም ሆነ ሕገ ደንባችን እንዳይነካ ከወዲሁ ተስማምተናል ብለዋል።

የተገኙ ድሎችን ማንኳሰስና ማንቋሸሽ እንዲቀርም ፍላጎታቸው መሆኑን በዚሁ ቃለ ምልልስ አንጸባርቀዋል።

ትምህክተኛው ሃይል ይህንን ስርአት ለማፍረስና ወደ ኋላ ለመመለስ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ይህንን ለመመከት ሕዝቡ ዝግጁ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ከዛሬ ረቡዕ መስከረም 16/2011 ጀምሮ በሚያካሂደው ጉባኤ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በፌደራሉ መንግስት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸውና በወንጀል የሚፈለጉት የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በአሁኑ ወቅት የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ሲሆኑ እንደገና ይመረጡ አይመረጡ ከወዲሁ የታወቀ ነገር የለም።