በኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየው ውይይት ያለውጤት ተጠናቀቀ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 17/2011) በኢትዮጵያና በግብጽ እንዲሁም በሱዳን መካከል ሲካሄድ የቆየው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁን የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር ገለጹ።

የሕዳሴውን ግድብ መሙላት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሊጠብ ባለመቻሉ ስብሰባው የተጨበጠ ውጤት እንዳልተገኝበትም አመልክተዋል።

የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር ሚስተር ሙሐመድ አብዱል አቲ ለግብጽ መንግስታዊ የዜና አገልግሎት መና እንደተናገሩት ሶስቱ ሐገራት የተጨበጠ ነገር ላይ ባይደርሱም ቀጣይ ስብሰባዎችን ለማድረግ ቁርጠኛ ናቸው።

የግድቡን ተጠባባቂ ውሃ የመሙላት ሁኔታ ዋናው ያለመግባባት ምክንያት መሆኑንም ግብጻዊው ባለስልጣን ገልጸዋል።

ሚኒስትሮቹ ትላንት ረቡዕ ያደረጉት ስብሰባ የውሃ አሞላሉ የግርጌ ሃገራትን በማይጎዳ መልኩ እንዴት ይከናወን የሚል እንደነበርም ተናግረዋል።

ግብጽ የግድቡን ውሃ ለመሙላት 15 አመታት ያህል ያስፈልጋል ስትል፣ኢትዮጵያ በግማሽ ባነሰ በ7 አመት ውስጥ ሊሆን ይገባዋል የሚል አቋም እንዳላት አንዳንድ ሪፖርቶች ያስረዳሉ።

በመጪው ጥቅምት ወር መጀመሪያ የግብጽ ወታደራዊ ልኡካን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ መዘገባችን ይታወሳል።

ልኡካኑ የሚመጡት ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።