በአፍ መፍቻ ቋንቋችን እንድንማር ይፈቀድልን ያሉ የራያ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቆሙ። በአድማው 23 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

በአፍ መፍቻ ቋንቋችን እንድንማር ይፈቀድልን ያሉ የራያ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቆሙ። በአድማው 23 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
( ኢሳት ዜና መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ/ም ) በዘንድሮ የ2011 ዓ.ም አዲሱ የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ገበታቸው መግባት የነበረባቸው የራያ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋችን ካልሆነ አንማርም ማለታቸውን ተከትሎ ከ1ኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ያሉ ትምህት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ዝግ ሆነዋል። ሕዝቡ በህገመንግስቱ የተሰጠን መብት የትግራይ ክልል ሊከለክለን አይገባም ብለዋል። አላማጣ ከተማን ጨምሮ እስከ 23 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች በሕዝቡ አቋም እንዲዘጉ መደረጋቸውን የራያ ሕዝብ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አዘዘው ሕዳሩ ገልጸዋል።
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ባልሆነ ቋንቋ አንማርም ማለታቸው ያስቆጣቸው የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ተማሪዎችን እና ወላጆችን የማባበል ሙከራዎችን ቢያደርግም አልተሳካለትም። ይህ ያስቆጣቸው የዞን ባለስልጣናት የትምህርት ቤቶችን ርዕሰ መምህራንን እና ምክትል ርዕሰ መምህራንን በመጥራት እናንተ የማግባባት እና በማኅበረሰቡ ላይ ጫና መፍጠር ባለመቻላችሁ ምክንያት የተፈጠረ አድማ ነው በማለት ማስፈራሪያና ተግሳጽ ተሰጥቷቸዋል። የትምህርት ቤቶቹ አስተዳዳሪዎቹ በበኩላቸው ከአሁን በኋላ ሕዝቡን ማስገደድ እንደማይችሉ እና እራሳችሁ ከፈለጋችሁ ማስገደድ ትችላላችሁ ሲሉ ለዞኑ ባለስልጣናት ምላሽ ሰጥተዋል።
ሕዝቡ በአንድ ላይ በቋሙ ስለጸና ትምህርት ቤቶቹ አልተከፈቱም። ከዚህ በኋላም በማኅበረሰቡ አቋም ምክንያት አይከፈትም ሲሉ አቶ አዘዘው ሕዳሩ አክለው አስታውቀዋል። የራያ ህዝብ በትግራይ ክልል የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰቶች መፍትሔ እንዲያገኙ የማንነት ኮሚቴ አዋቅረው ሕጋዊ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ እልባት ማግኘት አልቻሉም። ማኅበረሰቡ ከትግራይ ክልል ነጻ ለመውጣት የሚችልበትን
ፒቲሽን በመፈረም ሕጋዊ የፖለቲካ ጥያቄ በማቅረቡ በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል እና ፖሊስ የሚደርስባቸው ተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ሕዝቡን ከጅምላ እልቂት ለመታደግ እንዲቻል የማንነት አስመላሽ ኮሚቴው መከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ በአካባቢው እንዲገቡ ለጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።