በአፍሪካ ሙስናን መዋጋት ተስፋ አስቆራጭ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 23/2011)በአፍሪካ ሙስናን ለመዋጋት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ አስቆራጭ ነው ሲል ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

በሙስና ጉዳይ ላይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥናት የሚያደርገው ተቋም ይፋ እንዳደረገው የአፍሪካ ሀገራት አሁንም በሙስና ግንባር ቀደም ሆነው ቀጥለዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ሙስና የተንሰራፋባቸው ሃገራት በአብዛኛው በአፍሪካ ይገኛሉ ብሏል ተቋሙ።

ሶማሊያ ሙስና ስር የሰደደባት በመባል በቀዳሚነት ስትጠቀስ ደቡብ ሱዳን ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ቦትስዋናና ሲሼልስ አንጻራዊ መሻሻል ያሳዩ ሀገራት ተብለዋል።

የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የ2018 ሪፖርት አፍሪካን ሙስና የተንሰራፋባት አህጉር ሲል በቀዳሚነት አስቀምጧታል።

የ2018 የጥናት ግኝቱን በአጭሩ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሲል ነው የገለጸው።

ተቋሙ በሙስና ግንባር ቀደም የሆኑ የአፍሪካ ሃገራትን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ እንደገለጸው  በአለም አቀፍ ደረጃ ሙስና የተንሰራፋባቸው ሃገራት በአብዛኛው በአፍሪካ አህጉር ይገኛሉ ብሏል።

የአፍሪካ ሀገራት ሙስናን ለመዋጋት ቃል ገብተው ዘመቻ ቢከፍቱም ውጤቱ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።

ከአፍሪካ ሃገራት መካከል ሶማሊያ በአንደኛ ደረጃ ሙስና የተንሰራፋባት ሃገር እንደሆነች ተቋሙ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ተመልክቷል።

በተቋሙ ጥናት ከተካሄደባቸው 49 የአፍሪካ ሃገራት መካከል በሙስና የተለያዩ መለኪያዎች ከ43 በመቶ በላይ ውጤት ያሳዩት 8 ሃገራት ብቻ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ ስር የሰደደባቸውና መሻሻል ማሳየት ያቃታቸው እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።

አብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ሙስናን ስለመዋጋታቸው እየገለጹ መሆኑን የሚጠቅሰው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ውጤቱ ተስፋ ከማስቆረጥ ባለፈ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ይላል።

ማዕከላዊ መንግስት ሳይኖራት ለዓመታት የዘለቀችው ሶማሊያ በአንደኝነት ስትጠራ ፣ደቡብ ሱዳን ሁለተኛ ደረጃን መያዟን ሪፖርቱ አመላክቷል።

ሶማሊያ በዓለም ደረጃ ሙስና የተንሰራፋባት ተብላ በአንደኝነት ስትቀመጥ ከመለኪያው መቶ ነጥብ 10 ብቻ በማግኘት መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።

ሶማሊያ የሙስና አውራ በመባል ስትጠራ በተከታታይ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑም ተመልክቷል።

ሱዳን ሊቢያና ጊኒቢሳዎ እስከአምስተኛ ደረጃ ይዘው ሙስና የተንሰራፋባቸው ሃገራት ተብለዋል።

በአንጻሩ ሲሸልስ 61፣ ቦትስዋና እና ኬፕ ቨርዲ 57 ነጥብ በማስመዝገብ ሙስና እየቀነሰ የመጣባቸው ሃገራት ተብለው ተሰይመዋል።

ሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ያልቻሉ ሃገራት በሙስና የመጠቃት እድላቸው ሰፊ ሆኖ ተገኝቷል።

የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ስር በሰደዱባቸው ሃገራት ሙስናን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት ውጤት ማምጣት አልቻለም ሲል አትቷል።

ሙስናን ለመዋጋት የሚረዱ ተቋማት ደካማ መሆናቸውም ለሙስና መንሰራፋት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።

.