በአፋር ክልል ከአርታሌ የሚወጣው የጨው ክምችት “የመቀሌ ጨው” እየተባለ ለገበያ መቅረቡ በአፋር አክቲቪስቶች ዘንድ ቁጣ ቀሰቀሰ

ሰኔ ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሰባ አቶ ገአስ አህመድና አክቲቪስት አካድር ኢብራሂም በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት በአርታሌ፣ በዳሎል እና በሌሎች ከፍተኛ የጨው ክምችት የሚገኙባቸው የአፋር ቦታዎች ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ በጨው ማምረት ኢንቨስትመንት የተሰማሩት በሙሉ የህወኃት ደጋፊዎች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ናቸው።
ባለሀብቶቹ ከአርታሌና አካባቢው በየዓመቱ በሚሊዮን ኩንታል የሚገመት ጨው በማውጣትና በመቀሌ ባቋቋሙት የጨው ፋብሪካ በማዘጋጀት አጠቃላይ የሀገሪቱን የጨው ገበያ ከመሸፈን አልፈው ለጎረቤት ሀገራት እስከማቅረብ የደረሱ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ጨው ያወጡ የነበሩ በርካታ የአፋር ተወላጆች ያለምንም ካሳ ከመተዳደሪያ ሥራቸው እንዲወገዱ ተደርገዋል።
እንዲሁም አንድ የውጪም ይሁን የሀገር ውስጥ ባለሀብት በአንድ አካባቢ በኢንቨስትመንት በሚሰማራበት ወቅት የአካባቢው ተወላጆች በነሱ አቅም ሊሰሩ በሚችሉና ከፍተኛ ሙያቂ አቅም በማይጠይቁ ዝቅተኛ የሥራ መደቦች ላይ መሥራት እንዳለባቸው የኢንቨስትመንት አዋጁ ቢደነግግም፣ የጨው ማምረት ተግባሩ በሚጠይቀው የጉልበት ሥራ ላይ ጭምር የተሰማሩት ከትግራይ ክልል የመጡ ሠራተኞች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
ከአፋር ክልል ለሚወጣ ጨው ፋብሪካውንም እዚያው በአቅራቢያው ማቋቋም ከትራንስፖርት ጀምሮ በርካታ ወጪዎችን በማዳን በኩል ብዙ ጥቅም ቢኖረውም ፋብሪካውን አፋር ውስጥ አለመቋቋሙ ሀገሪቱም ሆነ ክልሉ ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢ ጥቅም እንዳያገኝ ማድረጉን የኢንቨስትመንት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ባለሀብቶቹ ከአፋር ክልል ለሚያወጡት ጨው ግብር የሚከፍሉት ለትግራይ ክልላዊ መንግስት ነው።
ከዚህ ሁሉ በላይ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን ባለሀብቶቹ ከአፋር ክልል ያመረቱትን ጨው ለገበያ የሚያቀርቡት በመቀሌ እንደተመረተ ጨው አድርገው ነው ያሉት አቶ ገአስና አቶ አካድር፤ በፌዴራሊዝም ስም በአፋር ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ብዝበዛና በደል ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል።
አቶ ገአስና አክቲቪስት አካድር ያደረሱን የምስል ማስረጃ እንደሚያመለክተው ከአፋር ክልል እየወጣ በመላው ኢትዮጵያ ለገበያ የሚቀርበው የገበታ ጨው ላይ ያለው ጽሁፍ በእንግሊዝኛና በአማርኛ “ሸዊት ጨው አቅራቢ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የገበታ ጨው፣ ዋና መሥሪያ ቤት ኢትዮጵያ፣ትግራይ፣መቀሌ። ማምረቻ ፋብሪካ መቀሌ፣ አዮዲናይዝ የገበታ ጨው”ይላል።”
በጽሁፉ ላይ ቢያንስ ጨው የሚወጣበት ቦታ እንኳ አለመጠቀሱ እጅግ ያሳዝናል ያሉት አቶ ገአስ፤ የአፋርን ጨው የትግራይ ጨው ብሎ መሸጥ በፌዴራሊዝም ስም እየተደረገ ያለው ዝርፊያ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለመደው የሀገራችን ፋብሪካዎች አሠራር ከነ አምቦ ውሃና፣ ጦሳ ውሃና ቡሬ ውሃ ጀምሮ በርካታ ፋብሪካዎች የምርታቸውን ምንጭ እንደሚጠቅሱ ይታወቃል።